
ደባርቅ: መጋቢት 4/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በሰሜን ጎንደር ዞን ለሁለት ዓመታት በነበረው ጦርነት በርካታ ወገኖች ሃብት እና ንብረታቸውን አጥተው እስካሁንም የሰው እጅ የሚያዩ ወገኖች አሉ።
ከእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ እነዚህ ወገኖች ጦርነት ካደረሰባቸው ጉዳት ሳያገግሙ በዞኑ ድርቅ ተከስቶ ችግራቸውን አባብሶታል። ይህን ተከትሎ ነዋሪዎችን ከሕልፈት እና ከችግር ለመታደግ በርካቶች በገንዘብ እና በምግብ ለመደገፍ ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።
ከእነዚህ ውስጥ በሰሜን አሜሪካ የተመሠረተው ዋልያ በጎ አድራጎት ማኅበር በጦርነት እና በድርቅ ለተጎዱ እንዲሁም ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች በሰሜን ጎንደር ዞን በኹሉም ወረዳዎች ተዟዙሮ እየደገፈ ይገኛል።
ማኅበሩ በሰሜን ጎንደር ዞን አዳርቃይ እና ማይጠብሪ ከተማ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች የምግብ እህል ድጋፍ አድርጓል። የማኅበሩ የሀገር ውስጥ አስተባባሪ ሙሉቀን አዛናው ማኅበሩ በዞኑ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ከዚህ ቀደም በሁለት ዙር ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል።
አሁን ደግሞ የማኅበሩ አመራሮች እና አባላት በማኅበራዊ ሚዲያ ባሰባሰቡት 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር 200 ኩንታል የምግብ እህል በአዳርቃይ እና ማይጠብሪ በሰሜኑ ጦርነት ጉዳት ደርሶባቸው አሁንም በችግር ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች ሦስተኛ ዙር ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
የአዳርቃይ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ምክትል ኀላፊ ፈንታሁን አጥናፉ በወረዳው በጦርነቱ ምክንያት አሁንም ችግር ውስጥ ያሉ ነዋሪዎች እንደሚገኙ ጠቁመዋል። በዋልያ በጎ አድራጎት የተደረገውን የ100 ኩንታል የምግብ ድጋፍ በከፍተኛ ችግር ውስጥ የሚገኙትን በመለየት ለጊዜያዊ ችግራቸው መድረስ ተችሏልም ብለዋል።
የማይጠብሪ ከተማ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሰለሞን ዩሐንስ በከተማዋ በጦርነት ሃብታቸውን ያጡ፣ ከሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች እና ከሱዳን ተፈናቅለው የመጡ እንዲሁም በችግር ውስጥ የሚገኙ ወገኖች መኖራቸውን አመላክተዋል።
ዋልያ በጎ አድራጎት ማኅበር ያደረገውን ድጋፍ የእለት ጉርስ ለሌላቸው ወገኖች ቅድሚያ በመስጠት ማሰራጨታቸውን ተናግረዋል።ድጋፍ የተደረገላቸው ወገኖች የሚያገኙት ድጋፍ አነስተኛ በመኾኑ ከፍተኛ ችግር ውስጥ መክረማቸውን አመላክተዋል። ዋልያ በጎ አድራጎት ማኅበር በችግር ላይ እያሉ መድረሱን ገልጸው ምሥጋና አቅርበዋል። ሌሎች አካላትም ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፡- አድኖ ማርቆስ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!