
ባሕር ዳር: መጋቢት 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ታሪክ እንደ ብራና ተገልጦ የሚነበብባቸው፣ ባሕል ሳይበረዝ የሚታይባቸው፣ ጥበብ እንደ ማለዳ ጀምበር የሚፍለቀለቅባቸው፣ እውቀት እንደማይነጥፍ አፍላግ የሚፈስስባቸው አያሌ ታሪካዊ ሥፍራዎች፣ ባሕላዊ ክዋኔዎች፣ ሃይማኖታዊ ክብረ በዓላት ያሉበት፤ አንድ እርምጃ በተራመዱ ቁጥር ታሪክ የሚማሩበት፣ እሴት የሚገበዩበት፣ ሃይማኖትን የሚያዩበት እና የሚሰሙበት፣ ከዳር እስከ ዳር ታሪክ ያለው ምድር ነው የአማራ ክልል፡፡
በተራመዱ ቁጥር ታሪክ ይማራሉ፤ ጆሮን ባዘነበሉ ቁጥር እጹብ የሚያሰኘውን ይሰማሉ። እጅን በዘረጉ ቁጥር የተበዋን ይዳስሳሉ፤ ያማረውን ማዕዛ ያሸትታሉ። ስለ ምን ቢሉ በታሪክ የተዋበ፣ በሃይማኖት የተሞሸረ፣ በባሕል ያጌጠ ምድር ነውና፡፡ ጎብኚዎች መዳረሻ ያደርጉት ዘንድ ይፈልጉታል፤ ይጓጉለታልም፡፡
አማራ ክልል አባቶች እና እናቶች ሠርተው ያስቀመጡት፣ ልጆች እንዲበሉት ያዘጋጁት የአማረ ማዕድ ሞልቶታል፡፡ ዳሩ ምን ያደርጋል ልጆች ማዕዱን መብላት ተሳናቸው፡፡ የሰላም ማጣት ማዕዱን ዘጋው፣ አላስቆርስ፣ አላስቀምስ አለው፡፡ የሰላም እጦት የቆዬውን ታሪክም አያስጠብቅም፡፡ አዲስ ታሪክ ለመሥራት፣ ታሪክንም ለመጠበቅ ሰላም ግድ ይላል፡፡ በአማራ ክልል በተደጋጋሚ በተፈጠረው የሰላም እጦት ምክንያት ጎብኚዎች ቀርተዋል፤ የቱሪዝም እንቅስቃሴውም ቀዝቅዟል፡፡ በክልሉ የተፈጠረው ግጭትም ቱሪዝሙን ጎድቶታል፡፡
የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኀላፊ ዓባይ መንግሥቴ ኢትዮጵያ የዓለም የቱሪዝም መዳረሻ ናት፣ በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ አቅጣጫዎች በተጓዙ ቁጥር ሃይማኖታዊ፣ ታሪካዊ እና ባሕላዊ ሀብቶች አሉ ይላሉ፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የሚገኙ፣ የጎብኚዎችን ቀልብ የሚስቡ ተፈጥሯዊ ሀብቶችም እንዳሉ ይገልጻሉ፡፡
የአማራ ክልል ደግሞ ላቅ ያለ ሃይማኖታዊ፣ ታሪካዊ እና ባሕላዊ የቱሪዝም ሀብቶች ያሉት ነው፤ ክልሉ ሰፊ ጸጋ ያለው መኾኑንም ነው የተናገሩት፡፡ በአማራ ክልል የሚገኙ ጸጋዎች የማንነት፣ የታላቅነት መገለጫ፣ የትውልዱ ማስተማሪያ እና መገንቢያ፣ የሞራል ልዕልና መለኪያ ኾነው የሚያገለግሉ ናቸው ይሏቸዋል፡፡ እነዚህ የበዙ ጸጋዎች የጎብኚዎችን ቀልብ በመሳብ የምጣኔ ሀብት ምንጭ የሚኾኑ፣ የሥራ እድል የሚፈጥሩ ሰፊ ሀብቶች ናቸው ነው የሚሉት፡፡
ቱሪዝም የሰዎችን እንቅስቃሴ የሚያይ እና የሚፈልግ ነው የሚሉት ምክትል ኀላፊው ጎብኚዎች ለጤና፣ ለምርምር፣ ለስፖርት፣ ለሃይማኖታዊ እና ለባሕላዊ ክብረ በዓላት ሊንቀሳቀሱ ይችላሉ፤ ሲንቀሳቀሱ ደግሞ ሀብት ይዘው ይንቀሳቀሳሉ፤ በዚህ ጊዜ እጅግ አስተማማኝ የኾነ ሰላም ይፈልጋሉ ይላሉ፡፡ አስተማማኝ ሰላም በሌለበት አካባቢ ሰው ገንዘብ ይዞ ሊንቀሳቀስ አይችልም፤ ሰዎች ካልተንቀሳቀሱ ደግሞ ቱሪዝም የለም ነው የሚሉት፡፡ አንዳንድ ሥራዎችን በሰላም እጦት ውስጥ ኾኖ መሥራት ይቻል ይኾናል፤ ቱሪዝም ግን ያለ ሰላም የሚታሰብ አይደለም፤ የአማራ ክልል ያለውን ጸጋ እንዳይጠቀም የሰላም እጦት ፈተና ኾኖበታል ነው ያሉት፡፡
አስቀድሞ ገና የኮሮና ቫይረስ የሰበረውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ለማነቃቃት ሲሠራ በነበረበት ወቅት የሰሜኑ ጦርነት ተከሰተ፣ ጦርነቱ ሲቋጭ በአማራ ክልል የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ተከተለ፤ ይሄም የክልሉን ቱሪዝም በእጅጉ ፈተነው፡፡ በሰሜኑ ጦርነት በርካታ መሠረተ ልማቶችን እና የቱሪዝም መዳረሻዎች ተዘርፈዋል፤ ወድመዋል፤ ይሄም በቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩ ወገኖችን ጎዳቸው፡፡
ከሰሜኑ ጦርነት ማግሥት በተገኘችው ሰላም የክልሉ ቱሪዝም በእጅጉ ተነቃቅቶ እንደነበርም አንስተዋል፡፡ በክልሉ የደረሱት ችግሮች ዘርፉን ለከፋ ጉዳት ዳርጎታልም ነው ያሉት፡፡ የክልሉ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ በችግር ውስጥም ኾኖ ታሪክ እንዲጠበቅ፣ ባሕል እንዳይበረዝ፣ ቅርሶች እንዲጠበቁ የማድረግ ሥራ መሥራቱንም አንስተዋል፡፡
በክልሉ በ2016 በጀት ዓመት በስድስት ወራት 6 ሚሊዮን የሀገር ወስጥ ጎብኚዎች፣ 27 ሺህ የሚኾኑ ደግሞ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ክልሉን ይጎበኛሉ ተብሎ ታቅዶ እንደነበር ያስታወሱት ምክትል ኀላፊው የታቀደውን እቅድ ማሳካት ባይቻልም በስድስት ወራት 4 ነጥብ 1 ሚሊዮን የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች፣ ከ10 ሺህ 500 በላይ የውጭ ጎብኚዎች መጎብኘታቸውን ነው የተናገሩት፡፡ በፈተና ውስጥም ኾኖ በስድስት ወራት ውስጥ 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ገቢ መገኘቱንም አመላክተዋል፡፡ ከታቀደው እቅድ አንጻር ግን ትንሽ ገቢ ነው፡፡ ሰላም ኖሮ ቢኾን ደግሞ ጠቀም ያለ ገንዘብ ወደ ክልሉ ይገባ ነበር ነው ያሉት፡፡
በቡሄ፣ በሶለል፣ በአሸንድዬ፣ በሻደይ፣ በግሸን ደብረከርቤ፣ በልደት፣ በጥምቀት፣ በአገው ፈረሰኞች በዓል፣ በቅዱስ መርቆሬዎስ በዓላት በርካታ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ወደ ክልሉ መጥተዋል፡፡ ኢምባሲዎች እና የቱሪስት አማካሪዎች የአማራ ክልል እንዳይጎበኝ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያዎችን ያቀርቡ ስለነበር የውጭ ሀገራት ጎብኚዎችን ቀንሷል፤ ያም ኾኖ በራሳቸው ተነሳሽነት የሚመጡ ጎብኚዎች ነበሩ፣ አሉም፡፡ የውጭ ሀገር ዜጎች መጎብኘታቸው ለክልሉ ቱሪዝም መነቃቃት የራሱ አስተዋጽኦ እንዳለውም ገልጸዋል፡፡
4 ነጥብ 1 ሚሊዮን የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ክልሉን ጎበኙት ሲባል የሚያጣጥሉ እና ነገሩን በሌላ መንገድ የሚረዱ አሉ የሚሉት ምክትል ኀላፊው ይሄ አስተሳሰብ የመነጨው ጎብኚ የሚለውን ጽንሰ ሀሳብ ካለመረዳት ነው ይላሉ፡፡ ጎብኚ ከ24 ሰዓታት ያላነሰ፣ ከአንድ ዓመት ያልበለጠ በሃይማኖታዊ፣ በጤና፣ በምርምር፣ በስፖርት እና በሌሎች ምክንያቶች የሚንቀሳቀሱ ሰዎችን ያካትታል ነው የሚሉት፡፡ ወደ ክልሉ የሚገቡ ጎብኚዎች መረጃ እንደሚያዝም አንስተዋል፡፡ በክልሉ የተፈጠረው የሰላም እጦት በቱሪዝም ሊገኝ የነበረውን ሀብት አስቀርቷል፡፡
ግጭቶች በሀገር በቀል መፍቻ መንገዶች እንዲፈቱ እና ቅርሶች እንዲጠበቁ እንደሚሠሩም አንስተዋል፡፡ ግጭትን በአባቶች ወግና ሥርዓት ለመፍታት መሥራት ይገባል ነው ያሉት፡፡ ጥገና የሚገባቸው ቅርሶች እንዲጠገኑ ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በመኾን እየሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ ያልታዩት እንዲታዩ፣ የታዩት ይበልጥ እንዲጎበኙ፣ ጥገና የሚያስፈልጋቸው እንዲጠገኑ ሰላም ወሳኝ ነው፤ ሰላም ከሌለ ሁሉም ነገር የለምና ብለዋል፡፡
የሰላም እጦት የዘጋውን ማዕድ፣ አላስቆርስ፣ አላስጎርስ ያለውን ሕብስት ሰላምን አምጥቶ፣ ችግሮችን በውይይት ፈትቶ ከማዕዱ መቅመስ፣ ከሕብስቱ መጉረስ ይገባል፡፡ ማዕድ እያለ ተራብኩ፣ ሕብስት ሳይጠፋ ተቸገርኩ ቢሉት የማይኾን ነውና፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!