
አዲስ አበባ: መጋቢት 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ)”በእንተ ስማ ለማርያም ለእኔ ተማሪ” የሚል ስያሜ የተሰጠው ፕሮጀክቱ በቁስቋም ቅድስት ማርያም መንፈሳዊ ማኅበር አማካኝነት የሚተገበር ነው።
ማኅበረ ቁስቋም የተለያዩ መንፈሳዊ እና ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን በመንደፍ ሥራዎችን እየሠራ የሚገኝ ተቋም እንደሚገኝ ገልጿል።ማኅበሩ በሱስ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶችን በዕውቀት እና በክህሎት ማብቃት፤ የተዘጉ አብያተ ክርስቲያናትን በማስከፈት፣ ገዳማትን መደገፍ፣ በሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ በኾኑ አደጋዎች ምክንያት በተለያዩ ችግሮቸ ውስጥ የሚገኙ ገዳማትን እና አድባራትን በማቋቋም የኢኮኖሚ ነጻነት እንዲኖራቸው ማድረግ፤ ለሴት መነኮሳት እና ለአቅመ ደካማ አረጋዊ መነኮሳት የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ማሟላት እንዲሁም የህክምና አገልግሎት የመስጠት ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ለዘመናት ጥንታዊውን የአብነት ትምህርት ቤትን ይዛና ጠብቃ አሁን እስካለንበት ትውልድ ማድረስ የቻለች ቤተክርስቲያን ናት፡፡
የብዙ ጥበብ መፍለቂያ የኾነው የአብነት ትምህርት ቤት ውስጥ የሚያገለግለው የግእዝ ቋንቋ ጥልቅ እና ሰፊ ምስጢራትን የያዘ ባለፀጋ ቋንቋ ነው፡፡
ነገር ግን ይህ የሀገር ሀብት የኾነው ቋንቋ የቤተክርስቲያን ንብረት ብቻ ተደርጎ ከተወሰደ ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡ ይህም ተግባር ማንነትን የዘነጋ ትውልድ ስለመኖሩ ማሳያ ነው ተብሏል።
ማኅበረ ቁስቋም ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት በሰሜኑ እና በደቡብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ያሉ የአብነት ትምህርት ቤት ዙሪያ በርካታ ሥራዎችን ለመሥራት እቅድ ማቀዱ ተነስቷል፡፡
ለዚህም “በእንተ ስማ ለማርያም ለእኔ ተማሪ” በሚል መሪ መልእክት ከመጋቢት 4 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ የዘመቻ ሥራዎቹን እንደሚጀምር የሱማሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ በተገኙበት ገልጿል፡፡
ማኅበሩ የቤተክርስቲያኗን ዶግማ እና ቀኖና በጠበቀ መልኩ በሀገራዊ ጥናት እና ምርምር የሚዘጋጅ ዶክመንተሪ ለማቅረብ ስለመታሰቡ ነው የተገለጸው፡፡በዘመመ የሳር ጎጆ ውስጥ ለሚገኙ ሁለት የአብነት ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች እና የመምህራን ማረፊያ ፣ የመማሪያ ጉባኤ ቤት፣ የምግብ ማብሰያ፣ የተሟላ ቤተ-መጽሐፍት፣ የማምረቻ ሼድ ግንባታ ከሙያዊ ሥልጠና ጋር መገንባት፣ በሀያ የአብነት ትምህርት ቤት ውስጥ ለሚገኙ ለ1ሺህ 200 የአብነት ተማሪዎች የሁለት ዓመት ቀለብ እና አልባሳት የማሰባሰብ እንዲሁም የሊቃውንት መምህራን ደምወዝ ክፍያ መፈጸም ላይ ማኅበሩ እንደሚሠራም ነው የተገለጸው፡፡
በአብነት ትምህርት ቤቶች አስከፊ የኾነውን ተላላፊ በሽታ ታሳቢ በማድረግ የሙሉ ጤና ምርመራ የሙያ ፍቃድ ባላቸው ብቁ የጤና ባለሙያዎች ለማድረግ ማኅበሩ ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን ገልጿል።
ማኅበሩ በገዛ ሀገሩ ተናጋሪ ያጣውን የግእዝ ቋንቋን በመታደግ ሂደት ውስጥ አሻራን ለማሳረፍ የራሳችንን አንድ ተማሪ እናስተምር የሚል ጥሪ አቅርቧል፡፡
ዘጋቢ፡- ድልነሳ መንግሥቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!