ተላላፊ ያልኾኑ በሽታዎችን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር እየሠራ መኾኑን የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ አስታወቀ።

16

ጎንደር: መጋቢት 4/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ተላላፊ ያልኾኑ በሽታዎች በተለይም ከልብ እና ደም ስር ጋር የተያያዙ (የካንሰር፣ የስኳር በሽታ እና ከመተንፈሻ አካላት ጋር የተያያዙ ህመሞች) በከፍተኛ ደረጃ እየጨመሩ እና የህመም፣ የሞት እና የአካል ጉዳት መንስኤ እየኾኑ መምጣታቸውን የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ ተወካይ ኀላፊ መልኬ መኮነን ነግረውናል።

ተላላፊ ያልኾኑ በሽታዎች የኑሮ ዘይቤን ተከትሎ የሚከሰቱ በመኾናቸው ግንዛቤን መፍጠር መቻል ችግሩ ከመከሰቱ በፊት ቀድሞ ለመከላከል የሚያስችል መኾኑን አስረድተዋል፡፡
አቶ መልኬ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የመከላከል እና የመቆጣጠር ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል። ለዚህም በከተማዋ በሚገኙ የጤና ተቋማት ከ80 በመቶ በላይ የመድኃኒት አቅርቦት መኖሩን ተናግረዋል።

ጤናማ ያልኾነ የአኗኗር ዘይቤ መከተል፣ ጤናማ ያልኾነ አመጋገብ፣ በቂ ያልኾነ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ፣ አልኮል አብዝቶ መጠቀም፣ ትምባሆ፣ ጫት መቃም እና ሌሎች እጾችን መጠቀም ተላላፊ ላልኾኑ በሽታዎች አጋላጭ ምክንያቶች መኾናቸውን በጎንደር ጤና ጣቢያ ተላላፊ ያልኾኑ በሽታዎች ክትትል ባለሙያ ሲስተር ጥሩየ ነጋ አብራርተዋል።

ህክምና ለማግኘት ለሚመጡ ተገልጋዮች የግንዛቤ ፈጠራን ጨምሮ ሌሎችም የህክምና አገልግሎቶች እንደሚሰጡም ሲስተር ጥሩየ አንስተዋል።በጎንደር ከተማ አሥተዳደር በጎንደር ጤና ጣቢያ የህክምና አገልግሎት ላይ ያገኘናቸው ተገልጋዩች ቅድመ መከላከል ላይ መሥራት አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡ ህመሙ ከተከሰተ በኋላም የህክምና ባለሙያዎችን ምክር ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ እንደኾነ ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡- ቃልኪዳን ኃይሌ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ለመጀመሪያ ጊዜ በሚወስዱት ፈተና የተሻለ ውጤት ለማምጣት እየተዘጋጁ መኾኑን ተማሪዎች ተናገሩ።
Next articleየግእዝ ቋንቋን ለትውልድ ለማሻገር እና የአብነት ትምህርት ቤቶችን ለመታደግ የሚያስችል የሁለት ዓመት ንቅናቄ ተጀመረ።