
ሁመራ: መጋቢት 4/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ለመጀመሪያ ጊዜ ለሚወስዱት ፈተና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ዝግጅት እያደረጉ መኾኑን የሁመራ ከተማ ተማሪዎች ተናግረዋል።
ተማሪ ሩት እና ተማሪ ሳሮን በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በሰቲት ሁመራ ከተማ አሥተዳደር የተከዜ አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ6ኛ እና የ8ኛ ክፍል ተማሪ ናቸው።
ተማሪዎቹ በ2016 የትምህርት ዘመን ለመጀመሪያ ጊዜ የሚሰጠውን የ6ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና እና የ8ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ዝግጅት እያደረጉ መኾኑን ነግረውናል።
በከተማቸው አንጻራዊ ሰላም በመኖሩ ትምህርታቸውን በአግባቡ እየተከታተሉ መኾኑንም ተማሪዎቹ አንስተዋል። በፈተና ጊዜ የተሻለ ውጤትን ለማስመዝገብ የጥናት መርሐ ግብር በማዘጋጀት እየተዘጋጁ እንደኾነም ተማሪዎቹ ተናግረዋል።
የተከዜ አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራን የማካካሻ ትምህርትን በመስጠት፤ ጥያቄዎችን አዘጋጅቶ በመስጠት ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ እገዛ እያደረጉ መኾኑን አንስተዋል።
የሁመራ ከተማ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ታሪኩ ዘውዱ በከተማዋ አምስት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንደሚገኙ አንስተው። ከ600 በላይ ተማሪዎችን የ6ኛ ክፍል ክልል አቀፍ እና የ8ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተናን ለማስፈተን እየተሠራ ነው ብለዋል።
በ2016 የትምህርት ዘመን በአንደኛው ወሰነ ትምህርት መምህራን ለተማሪዎች በሚሰጡት የማካካሻ ትምህርት እና የተለያዩ ድጋፎች የተማሪዎች ውጤት ላይ መሻሻል መታየቱን ገልጸዋል።
የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ እና ተማሪዎች ይበልጥ ውጤታማ እንዲኾኑ ወላጆች የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባም አሳስበዋል።በዞኑ በ2016 የትምህርት ዘመን ከ12 ሺህ 400 በላይ ተማሪዎች የ6ኛ እና የ8ኛ ክፍል ፈተና እንደሚወስዱ ከዞኑ ትምህርት መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
ዘጋቢ :- ያየህ ፈንቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!