የአካባቢ ወንጀል ችሎት ብቻ የሚስተናገዱባቸው ፍርድ ቤቶች ሊቋቋሙ ነው፡፡

21

ባሕርዳር: መጋቢት 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአካባቢ ጥበቃ ላይ እየተፈፀሙ ያሉ ወንጀሎችን ለመከላከል የአካባቢ የወንጀል ችሎት ብቻ የሚስተናግዱባቸው ፍርድ ቤቶችን ለማቋቋም ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለማጽደቅ እየተሠራ እንደኾነ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ገልጿል፡፡

የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ሕግ እና ደረጃዎች ዴስክ ተወካይ ኀላፊ መስፍን ታደሰ በአካባቢ ላይ እየተፈፀሙ ያሉ ወንጀሎችን ለመከላከል እና በአካባቢ ወንጀል መከላከል ዙሪያ የተደነገጉ የሕግ ማዕቀፎችን በሚፈለገው ልክ ተግባራዊ ለማድረግ የአካባቢ ጉዳዮችን ብቻ የሚያስተናግዱ ፍርድ ቤቶች መቋቋም አለባቸው፡፡

ፍርድ ቤቶች ከሚያስፈልጋቸው የሰው ኀይል ጋር ለማቋቋም እና የአካባቢ ወንጀልን የሚከላከሉ የተለያዩ የሕግ ድንጋጌዎችን በሚፈለገው ሕግ ተፈፃሚ ለማድረግ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለማፅደቅ እየተሠራ እንደኾነም ጠቁመዋል፡፡

የአካባቢ ብክለትን፣ የኬሚካል አያያዝን፤ የድምፅ ማጉያ አጠቃቀምን እና መሰል የአካባቢ ወንጀልን ለመከላከል የሚያስችሉ የተለያዩ የሕግ ማዕቀፎች እና ድንጋጌዎች ቢኖሩም አሁን አካባቢ ላይ እየደረሰ ካለው ወንጀል አንፃር በሚፈለገው ልክ ተግባራዊ እየኾኑ አይደለም ብለዋል፡፡

የአካባቢ ወንጀልን ለመከላከል የተደነገጉ የሕግ ማዕቀፎችን በሚፈለገው ልክ ተግባራዊ ለማድረግ እና ተጠያቂነትን ለማስፈን የአካባቢ ወንጀል ችሎት ለብቻ የሚስተናገዱባቸው ፍርድ ቤቶችን ለማቋቋም የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለማጽደቅና ሥራ ላይ እንዲውል የማድረግ ሥራ እየተሠራ እንደኾነም ተናግረዋል፡፡

አኹን ባለው የፍርድ ቤት አሠራር የአካባቢ ጉዳዮችን ብቻ የሚያስተናግዱ ችሎቶች የሉም ያሉት አቶ መስፍን የአካባቢ ጉዳዮች ችሎት ለብቻ በፍርድ ቤት እንዲታዩ አደረጃጀት የሚሠራ ረቂቅ አዋጅ ለማጽደቅ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

ረቂቅ አዋጁ የአካባቢ ወንጀሎች የሚዳኙበትን ችሎት አደረጃጀት ኹኔታን ከማሳየት ባለፈ ፍርድ ቤቶች የአካባቢ የወንጀል ተጠያቂነት ሥራን የተቀላጠፈ እንዲኾን ያደርጋል ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ረቂቅ አዋጁ ፍርድ ቤቶች፣ ዐቃቤ ሕጎች እና ፖሊሶች ስለአካባቢ ወንጀል ግንዛቤው ኖሯቸው እንደሌሎች ወንጀሎች ክስ እንዲመሠርቱ የሚያስችልም ነው ማለታቸውን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘግቧል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአፈር ማዳበሪያን ከጅቡቲ ወደብ ከክረምት በፊት ለአርሶ አደሩ ለማድረስ ጥረት እየተደረገ መኾኑ ተገለጸ፡፡
Next articleለአቶ ደመቀ መኮንን የምስጋና እና የክብር ሽኝት ተደረገላቸው።