
ባሕርዳር: መጋቢት 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ በበርካታ ለውጦች ውስጥ እያለፈ ያለውን የዓለም ጂኦ ፖለቲካ ባገናዘበ መንገድ በጥበብ እና በእውቀት የዲፕሎማሲ ሥራን ማከናወን እንደሚገባ ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት የሥራ ኀላፊዎች እና ሠራተኞች ጋር የትውውቅ እና የውይይት መርሐ ግብር አካሂደዋል።
አምባሳደር ታዬ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በተቋም ደረጃ የሠራተኞቹ አቅም እና ችሎታ እንዲኹም ተቋሙ በቀጣይ መከተል ስለሚገባው አቅጣጫዎች ገለጻ አድርገዋል።
ዲፕሎማቶች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች ለማስጠበቅ በየጊዜው የሚለዋወጠውን የዓለም ጂኦ ፖለቲካ ከግንዛቤ በማስገባት ራሳቸውን በሁሉም ዘርፍ በማብቃት መትጋት እንደሚገባቸውም ነው ያስገነዘቡት፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ሚኒስትሩ አምባሳደር ታዬ በተቋሙ ውስጥ ያለፉ እና በሚገባ የሚያውቁት በመኾናቸው ተቋሙን ወደ ተሻለ ከፍታ ለማሻገር ከፍተኛ አበርክቶ እንደሚኖራቸው ተናግረዋል። ሚኒስትር ዴኤታዋ አምባሳደር ብርቱካን ሁሉም ሠራተኛ በሙሉ አቅሙ መሥራት እንዳለበትም አሳስበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!