እርስ በእርስ መገዳደል እንዲቆም እና ማኅበረሰቡ ሰላሙን እንዲጠብቅ ብጹእ አቡነ መቃሪዮስ አሳሰቡ፡፡

24

ባሕርዳር: መጋቢት 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአዳርቃይ ወረዳ በሰሜኑ ጦርነት ከግለሰብ ንብረት ጀምሮ እስከ መንግሥት እና የሃይማኖት ተቋማት ድረስ ከፍተኛ ውድመት መድረሱ ይታወሳል። በወረዳው ውድመት የተፈጸመባቸው የእምነት ተቋማትን መልሶ ለመገንባት እና የአካባቢውን ሰላም ማስጠበቅ ላይ ያለመ ፕሮግራም ተካሂዷል።

በፕሮግራሙ የዞኑን ሀገረ ስብከት ወክለው የሶማሌ ክልል ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብጹእ አቡነ መቃሪዮስ ተገኝተዋል። ሊቀ ጳጳሱ በዚህ ወቅት እንዳሉት የወረዳው ነዋሪዎች በጦርነቱ ከፍተኛ ችግር እንደደረሰባቸው በማስታወስ የእርስ በእርስ መገዳደልን አቁመው፤ ሰላማቸውን በመጠበቅ ከችግር ለመውጣት እንዲሠሩ አሳስበዋል።

የወረዳው ወጣቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶችን ተግሳጽ በመቀበል ሰላማቸውን እንዲጠብቁ፤ የወደሙ የእምነት ተቋማትን እና የመንግሥት ተቋማትን በትብብር እንዲገነቡም ጠይቀዋል።

የአካባቢው የሃይማኖት አባቶች በበኩላቸው ጦርነት ትውልድን እንደሚያጠፋ፤ ቤተሰብን እንደሚበትን፤ ንብረትን እንደሚያወድም እና ከአካባቢ እንደሚያፈናቅል በነበረው ጦርነት ተመልክተናል ብለዋል። ስለኾነም ከምንም በላይ ለሰላም እንሠራለን ነው ያሉት።

በነበረው ጦርነት የግለሰቦች፣ የመንግሥት ተቋማት እና የእምነት ተቋማት ከፍተኛ ውድመት እንደደረሰባቸው ያነሱት የሃይማኖት አባቶቹ መንግሥት የጀመረውን የመልሶ ማቋቋም ሥራ አጠናክሮ በመቀጠል የውኃ፣ የመብራት፣ የጤና ተቋማት እና መሰል ችግሮችን ለመፍታት መሥራት ይኖርበታል ብለዋል።

አሚኮ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች እንዳሉት ጦርነት ኑሮን ከዜሮ እንዲጀምሩ አድርጓል፤ አሁንም ገና ከችግር አለመውጣታቸውንም አስገንዝበዋል። ጦርነት አንደማይፈልጉም ነው የገለጹት።

ጦርነት ካደረሰባቸው ችግር ለመውጣት ጥረት ላይ መኾናቸውን ያነሱት ነዋሪዎቹ መንግሥት የወደሙ የጤና፣ የውኃ፣ የትምህርት እና መሰል ተቋማትን መልሶ የመገንባት ሥራ እንዲሠራ፤ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ወገኖችንም እንዲረዳ ጠይቀዋል።

የአዳርቃይ ወረዳ አሥተዳዳሪ ሚሊዮን ታደሰ ማኅበረሰቡ ሰላም ወዳድ መኾኑ፤ የጸጥታ ኀይሉ ጥንካሬ እና የታጠቁ አካላት ወደ ሰላም መምጣት ለአካባቢው ሰላም መኾን አስተዋጽኦ አበርክተዋል ብለዋል።

የክልሉ መንግሥት ከዚህ ቀደም ለመልሶ ግንባታ በሰጠው በጀት የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቅሰው አሁንም ሰላሙን ተጠቅሞ መልሶ ግንባታውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

ዘጋቢ፡- አድኖ ማርቆስ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የምክክር መድረኩ ኀላፊነትን በአግባቡ ለመወጣት እና የሕዝብን ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችል የጋራ መግባባት የሚፈጥር ነው”
Next article”የዲፕሎማሲ ሥራን በጥበብ እና በእውቀት ማከናወን ይገባል” የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ