“የምክክር መድረኩ ኀላፊነትን በአግባቡ ለመወጣት እና የሕዝብን ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችል የጋራ መግባባት የሚፈጥር ነው”

25

ባሕር ዳር: መጋቢት 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ) “ፈተናዎችን በጽናት እና በቁርጠኝነት በመሻገር የሕዝባችንን ዘላቂ ሰላም እና ልማት እናረጋግጣለን” በሚል መሪ መልእክት የምክክር እና የውይይት መድረክ በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡

የፌዴራል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት እየተካሄደ በሚገኘው የምክክር መድረክ ከክልል እስከ ወረዳ የሚገኙ ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች እየተሳተፉበት ነው፡፡
በምክክር መድረኩ ላይ በክልሉ የተፈጠረውን የሰላም መደፍረስ ለመቀልበስ እና ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ የተሄደበት መንገድ በጥልቀት እየተገመገመ ነው ተብሏል፡፡

በሰላም እጦቱ ምክንያት በሰሜን ሽዋ ዞን ብቻ ከ12 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ተዘርፏል ያሉት የዞኑ ዋና አሥተዳዳሪ መካሽ ዓለማየሁ ከደረሰው ሰብዓዊ ጉዳት በተጨማሪ የማኅበራዊ ተቋማት ውድመት እና የምጣኔ ሀብታዊ እንቅስቃሴ መገታት ክልሉን በከፍተኛ ሁኔታ ጎድቶታል ብለዋል፡፡ በዞኑ አርሶ አደሮች መንግሥትን ትደግፋላችሁ በሚል ምክንያት ብቻ እንግልት ሲደርስባቸው እንደቆየም አንስተዋል፡፡

አሁን ላይ ሕዝቡ ነገሮችን በጥልቀት እየመረመረ ከእውነታው ላይ ደርሷል ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው ሕዝቡ በፈታኝ ወቅት ሳይቀር ላሳየው አስተውሎት የተሞላበት እርጋታ ምሥጋና ይገባዋል ብለዋል፡፡

በየደረጃው ያለው የመንግሥት አካል ሊመልሳቸው የሚገቡ ጥያቄዎች መኖራቸው ግልጽ ነው፤ ነገር ግን የሚመለሱበት መንገድ ሥልጡን እና ዋጋ የማያስከፍል ሊኾን ይገባው ነበር ነው ያሉት፡፡

ባለፉት ስምንት ወራት ፈተናዎችን ለመሻገር የተሄደባቸው እርቀቶች በምክክር መድረኩ በጥልቀት እየተገመገሙ ነው ያሉን ደግሞ የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንታይቱ ካሴ ናቸው፡፡

በቀሪ ጊዜያት ያለፉ እድሎችን በሚገባ ተጠቅሞ በክልሉ ያለውን አንጻራዊ ሰላም እንዲጸና ለማድረግ የፖለቲካ አመራሩ አረዳድ የተቀራረበ እንዲኾን ይፈለጋል ነው ያሉት፡፡
ክልሉ ተደቅኖበት የነበረው የሰላም መደፍረስ ችግር በሀገር መከላከያ ሠራዊት እና በክልሉ የፀጥታ መዋቅር ወደ አንጻራዊ መረጋጋት መጥቷል ያሉት የምክክር መድረኩ ተሳታፊዎች የክልሉን ሰላም ሙሉ በሙሉ ለማረጋገጥ የአመራር ቁርጠንነት ወሳኝ መኾኑን አንስተዋል፡፡

ጽንፈኝነት ለእርስ በእርስ ግጭት እና ዘረፋ እንደዳረገ የታዩ ምልክቶች በቂ ናቸው ያሉት አመራሮቹ የሕዝብን መከራ እና ስቃይ ከዚህ በላይ ማራዘም ተገቢ ባለመኾኑ በጋራ መሥራት ይገባል ብለዋል፡፡

የምክክር መድረኩ በተለያየ የክልሉ አካባቢ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ እንዲረዱ እና የጋራ አቋም እንዲይዙ እንዳገዛቸውም ነግረውናል፡፡ ኀላፊነትን ለመወጣት እና የሕዝብ ጥያቄን በአግባቡ ለመመለስ ከፌዴራል እስከ ወረዳ ያለው የመንግሥት መዋቅር በችግሮቹ ዙሪያ የተቀራረበ አረዳድ እና የጋራ ቁመና እንዲኖር ማስቻሉንም ጠቁመዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአረርቲ ከተማን የመጠጥ ውኃ ጥያቄው ለመመለስ እየተሠራ ነው ተባለ፡፡
Next articleእርስ በእርስ መገዳደል እንዲቆም እና ማኅበረሰቡ ሰላሙን እንዲጠብቅ ብጹእ አቡነ መቃሪዮስ አሳሰቡ፡፡