
ባሕርዳር: መጋቢት 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ የአረርቲ ከተማ አሥተዳደር ነዋሪዎች የንጹህ መጠጥ የውኃ እጥረት እንዳለባቸው ተናገሩ፡፡ የከተማ አሥተዳደሩ የንፁህ መጠጥ ውኃ ሽፋን 35 በመቶ ብቻ ነው፡፡ ይህም በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የነዋሪዎች ቁጥር በአግባቡ ተደራሽ ለማድረግ አዳጋች ኾኗል፡፡
የከተማዋ ነዋሪዎች ለአሚኮ በሰጡት ሀሳብም አኹን ላይ የውኃ ችግሩን መጋፈጥ ከሚችሉት በላይ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ በውኃ ችግር ዓመታት አለፉ የሚሉት ነዋሪዎቹ ለገጠማቸው ችግር መፍትሔ እንዲሰጣቸው የሚመለከታቸውን አካላት ጠይቀዋል፡፡
የከተማ አሥተዳደሩ ውኃና ፍሳሽ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት በሰጠው ምላሽ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ የሕዝቡን ችግር ለመፍታት አዳዲስ የውኃ ፕሮጀክቶች እየተሠሩ ነው፡፡ እነዚህ የውኃ ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ በአንድ ሴኮንድ ውስጥ አስከ 45 ሊትር ንጹህ የመጠጥ ውኃ ያመነጫሉ፡፡ የከተማውን ፍላጎትም በአግባቡ መሸፈን ይችላሉ፡፡
ይሁን እንጂ በተቀመጠላቸው ጊዜ መጠናቀቅ አለመቻላቸውን ነው የጽሕፈት ቤቱ ኀላፊ ወንድሙ ግርማ የገለጹት፡፡ ከግንባታ ተቋራጮች ጋር በመነጋገር በቅርቡ ለማጠናቀቅ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
የከተማውን የንጹሕ መጠጥ ውኃ ችግር ለመፍታት ነዳጅ መጠቀምን እንደ አማራጭ መጠቀም ተጀምሯል ያሉት ኀላፊው የሕዝቡን ፍላጎት ግን ማርካት እንዳልተቻለ አመላክተዋል፡፡ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትም የኀይል አቅርቦት ችግር መፈታት ይኖርበታልም ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት በበኩሉ የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስ በትኩረት እየሠራ ስለመኾኑ አስታውቋል፡፡ በአገልግሎቱ የደብረብርሃን ዲስትሪክት ዲስትሪቢዩሽን፣ ኦፕሬሽን፣ ኮነስትራከሽን እና ሜንቴናንስ ሥራ አሥኪያጅ ተክሌ አቡ እንዳሉት የመሥመር ዝርጋታ ሥራው ተጠናቅቋል፡፡ የትራንስፈርመር ሥራና የመንደር መስመር ዝርጋታ ሥራ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቁም አስረድተዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!