
ባሕርዳር: መጋቢት 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሰላም ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዱዓለም የተቋሙን የስድስት ወራት አፈጻጸም አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ፤ ዘላቂ ሰላምን በመገንባት እና የፌደራል ሥርዓትን ከማጎልበት አኳያ አበረታች ሥራ መሠራቱን ገልፀዋል።
በክልሎች መካከል ያለውን ግንኙነት የማጠናከር እና ግጭትን በመከላከል በኩልም የቅድመ መከላከል እና የፈጣን ምላሽ ሥራዎች መልካም አፈጻጸም የታየባቸው መኾኑን ጠቁመዋል።
መልሶ ማቋቋም በተመለከተ ባለፉት ስድስት ወራት ከተለያዩ አካባቢዎች በግጭት እና በተፈጥሮ አደጋ የተፈናቀሉ 111 ሺህ የሚኾኑ ዜጎች ወደ ቀያቸው መመለሳቸውን ገልፀዋል።
ይኹንና በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ኋላቀር የፖለቲካ ባህል አኹንም እንቅፋት እየፈጠረ መኾኑን ገልጸዋል። ይህ የፖለቲካ ባህል ከስረ መሰረቱ መቀየር እንዳለበት አንስተዋል። ከዚህ አንጻር በኃይል ሥርዓትን ለመቀየር የመሞከር አዝማሚያዎች ዛሬም መቀጠላቸውን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ የተቃኘው በዚሁ የመጠፋፋት መንገድ ነው ብለዋል። እስካሁን ድረስም እየተንከባለለ የመጣ የፖለቲካ ባህል ኾኗልም ነው ያሉት። የሀሳብ መለያየት ለመጠፋፋት ምክንያት ሊኾን እንደማይገባ ተናግረዋል።
ሀገሪቱን ወደ ግጭት አዙሪት የሚከታት ሚዛናዊነት የጎደለው ትርክትም ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ እንቅፋት እየፈጠረ መኾኑን አስረድተዋል። በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ውይይት ካልዳበረ የቱንም ያህል ግጭትን ማስቆም ቢቻል ነገ ላይ ግጭት እንደማይፈጠር ዋስትና እንደማይኾን አስረድተዋል። በመኾኑም ውይይትን መሰረት ያደረገ ፖለቲካ ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸው፤ ጎን ለጎንም ብዝኃነትን እና አብሮነትን መሰረት ያደረገ ትርክት ማጎልበት ይገባል ብለዋል።
በተለይም ገዥ ትርክቱ ቀደም ሲል የነበሩ ትርክቶች ያስከተሉትን ጉዳት በአግባቡ የፈተሸ እና ያንን ሊያርም የሚችል መኾን እንዳለበትም ነው ያስገነዘቡት። ምንም ዓይነት የሀሳብ ልዩነቶች ቢኖሩም ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ሁሉም በጋራ መቆም እንዳለበት ገልጸው፤ “ሲመች ኢትዮጵያ ሳይመች ደግሞ ኢትዮጵያ ለኔ ምኔ ናት” የሚል አመለካከት ተገቢ አለመኾኑን ተናግረዋል።
የመገናኛ ብዙኃን ሰላምን በማስፈን ያላቸውን ሚና በአግባቡ መወጣት እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበው፤ በተቃራኒው ችግሮች እንዲባባሱ የሚሠሩ ደግሞ ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ እንደሚገባም አሳስበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!