“ሀገራዊ የሰላም እጦቶችን ለመቅረፍ ከመንግሥት ባሻገር እንደዜጋ ሁሉም የበኩሉን መወጣት አለበት” የኢትዮጵያ የሰላም ተቋም

40

አዲስ አበባ: መጋቢት 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የኢትዮጵያ ሰላም ተቋም ከአሜሪካን ተራድኦ ድርጅት (ዩ.ኤስ.ኤ.አይ.ዲ) ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ ውስጥ እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶችን በእውነተኛ ውይይት የመፍታት ባሕልን ለማዳበር ተከታታይ የኾኑ መድረኮችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቶ በዛሬው ዕለት ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ውይይት እያደረገ ነው።

በአማራ ክልል ያለውን ችግር ለመፍታት የሚደረጉ የሰላም ጥረቶችን ማበረታታት በሚል እየተካሄደ ባለው የባለ ድርሻ አካላት የምክክር መድረክ የኢትዮጵያ የሰላም ተቋም የቦርድ ሰብሳቢ አምባሳደር ሙሉጌታ ኢተፋ (ዶ.ር) ንግግር አድርገዋል።

እየተደረጉ ያሉ ጦርነቶች ሀገራዊ ሃብት እና ዜጋውን ክፉኛ እየጎዱ መኾናቸውን ያነሱት የቦርድ ሰብሳቢው “ሀገራዊ የሰላም እጦቶቹን ለመቅረፍ ከመንግሥት ባሻገር እንደዜጋ ሁሉም የበኩሉን መወጣት አለበት” ብለዋል።

ሌላው በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የሰላም ግንባታ እና ብሔራዊ መግባባት ዘርፍ ሚኒስትር ድኤታ ከይረዲን ተዘራ(ዶ.ር) እንደ መንግሥት ችግሮችን በሰላም አማራጭ ብቻ የመፍታት ፍላጎት ውስጥ ነን እንዲህ መሰል የቅድመ ውይይት መድረኮችም ተጠናክረው መቀጠል ይገባቸዋል ብለዋል።

በዩ ኤስ ኤ አይ ዲ የዴሞክራሲ እና አሥተዳደር ቢሮ ዳይሬክተር ስቴፋኒ ጋርቬይ በኢትዮጵያ ያለው የሰላም እጦት ከፍተኛ ችግር እያስከተለ ነው ብለዋል። ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ተነጥለዋል፤ አርሶ አደሮችም ችግር ውስጥ ናቸው፤ እናቶች እና ሕጻናትም በችግሩ እየተፈተኑ ነው ብለዋል።

አሁን በአማራ ክልል እየኾነ ያለውም ይሄው ነው ያሉት ዳይሬክተሯ ከዚህ ችግር ለመውጣት እንደ ድርጅት ማኅበረሰቡን እና መንግሥትን መደገፍ እንፈልጋለን ብለዋል። ሀገራዊ መረጋጋት እና ሰላምን ለማምጣት በስፋት መሥራት እንፈልጋለን ብለዋል።

ከምንደግፍባቸው እና ከምናግዝባቸው መንገዶች አንዱ መሰል የውይይት መድረኮችን ማዘጋጀት እና መደገፍ ነው ያሉት ስቴፋኒ ጋርቬይ ሥራውን አጠናክረንም እንቀጥላለንም ብለዋል፡፡

በመድረኩ ከሰላም ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ምክክር ኮሚሽን፣ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ ከአማራ ክልል የፀጥታ ተቋማት፣ ከምሁራን እና ሌሎችም ባለ ድርሻ አካላት ተሳትፈውበታል።
የኢትዮጵያ ሰላም ተቋም እ.አ.አ በ1992 የተቋቋመ እና በኢትዮጵያ የሰላም ግንባታ እና ግጭት አፈታት ተግባራት የጥናት እና ምርምር እንዲኹም የተቋማት አቅም ማጎልበት ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል፡፡

ዘጋቢ፡- እንዳልካቸው እባቡ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየዋጋ ግሽበትን ለማረጋጋት መንግሥት የተለያዩ የመፍትሔ እርምጃዎችን እየወሰደነው ተባለ።
Next articleየኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አባቶች የዓድዋ ድል መታሰቢያን ጎበኙ።