
ባሕርዳር: መጋቢት 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ) መንግሥት የዋጋ ግሽበትን ለማረጋጋት የተናበበ የገንዘብ፣ የፊስካል እና የምርታማነት የፖሊሲ እርምጃዎችን እየወሰደ መኾኑን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ.ር) ገለጸዋል።
ለኢትዮጵያ ሕዝብ መሠረታዊ ችግር ከኾኑ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች አንዱ የዋጋ ግሽበት መኾኑ ይታወቃል። በተለይም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች የመግዛት አቅማቸው ዝቅተኛ በመኾኑ የዋጋ ግሽበት በሚፈጥረው ጫና ተጎጂዎች ኾነዋል። በመኾኑም የዋጋ ግሽበትን ለማረጋጋት መንግሥት የተለያዩ የመፍትሔ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ይገኛል።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ.ር) የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ እና በጀት ይፋ ሲደረግ የዋጋ ግሽበትን በመቆጣጠር የኑሮ ውድነትን ማረጋጋት አንዱ የትኩረት መስክ መኾኑን አንስተዋል።
ለዚህም በፊስካል ፖሊሲ ደረጃ ለዓመቱ የዘርፍ ተቋማት የተመደበው በጀት በአንጻራዊነት ካለፈው ዓመት ብዙም ጭማሪ ያልተደረገበት እና የዋጋ ግሽበትን ለማረጋጋት እንዲሠሩ የሚያስገድድ መኾኑን ገልጸዋል።
በውሳኔው መሠረት ተቋማት በአነስተኛ ወጪ ፍጥነት እና ፈጠራን በመጨመር ውጤት ያለው እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ እና በዲሲፕሊን እንዲመሩ ይኾናል። በመኾኑም የገንዘብ ሚኒስቴር በበጀት ዓመቱ ቀሪ ወራትም የበጀት አሠራሩን ጠበቅ እንዲያደርግ በመንግሥት ተወስኖ እየተሠራ ነው ብለዋል።
የዋጋ ግሽበቱን ለማረጋጋት የተናበበ የፖሊሲ እርምጃ እየተወሰደ ነውም ሲሉ አክለዋል። ብሔራዊ ባንክም የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያ በማድረግ ጥብቅ ውሳኔዎችን ማሳለፉን ጠቅሰዋል።
ለመንግሥት የሚሰጠውን የቀጥታ የብድር መጠን በእጅጉ በመቀነስ ባለፈው ዓመት ከተሰጠው ብድር አንድ ሦስተኛ እንዳይበልጥ እና መሠረታዊ በኾነ መልኩ እንዲገደብ ተደርጓል ብለዋል። ይህም ማለት የመንግሥት ወጪ እድገት እንዲገደብ፣ የበጀት ጉድለቱን ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት አኳያ እንዲቀንስ መደረጉን ተናግረዋል።
መንግሥት ከሀገር ውስጥ ባንኮች በተለይም ከማዕከላዊ ባንክ የሚወስደውን የብድር መጠን እንዲቀንስ መደረጉን አስረድተዋል። በምግብ ሸቀጦች ላይ ያለውን የዋጋ ግሽበት በዋናነት ለመፍታት ምርትና ምርታማነትን ማሳደግና የንግድ ሥርዓቱን ማሻሻል ወሳኝ መኾኑን አንስተዋል።
ለዚህም በሁለተኛው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ ለምርት ማደግ፣ ለንግድ ሥርዓቱ ሪፎርም ትኩረት ተሰጥቷል ነው ያሉት።በዘላቂነት የዋጋ ግሽበትንም ኾነ የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት የዜጎችን የመግዛት አቅም የማሳደግ፣ የምርት ዋጋ ላይ ትርጉም ያለው የዋጋ ቅነሳ ማድረግ ወሳኝ መኾኑን ጠቅሰው፤ አኹንም ለውጦች አሉ ብለዋል።
ክልሎች ለምርታማነት ማደግ እና ለምርት ዝውውር በትብብር መሥራት እንዳለባቸው ፤ የንግድ ቁጥጥር ተቋማትም የምርት ግብይት ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪን ሥርዓት በማስያዝ ለዋጋ ግሽበቱ መረጋጋት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጠይቀዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!