
ባሕር ዳር: መጋቢት 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ እና ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ከሌሎች የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ጋር በመኾን የለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካን የግንባታ ሂደት ተመልክተዋል። ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ከፕሮጀክቱ አመራሮች ጋር በነበራቸው ውይይት ፋብሪካው በአጭር ጊዜ ተጠናቅቆ ወደ ምርት እንደሚገባ ተገልጿል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ እያደገ ለመጣው የሀገሪቱ የግንባታ ዘርፍ በቂ የሲሚንቶ ግብዓት ለማቅረብ መንግሥት በትኩረት እየሠራ ስለመኾኑ ጠቁመዋል። በተለይም ለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ምርት ሲጀምር አሁን ለሚታየው የሲሚንቶ እጥረት ትልቅ እፎይታ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
ፋብሪካው በግንባታ ወቅት የሚያጋጥሙትን ችግሮች ሁሉ ተከታትለን በመፍታት እዚህ ማድረስ ተችሏል ሲሉም ተናግረዋል። “አሁን የለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ ግንባታ ምርት በመጀመር ሕዝብን ተጠቃሚ ለማድረግ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሷል” ሲሉም ገልጸዋል። የግንባታውን ዘርፍ እየፈተነ ያለውን የሀገራችንን የሲሚንቶ ገበያ ለማረጋጋት ትልቅ ፋይዳ ይዞ እንደሚመጣም ጠቁመዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አማራ ክልል ለሲሚንቶ ጥሬ እቃነት የሚውል እምቅ ሃብት እንዳለው አመላክተዋል። ይህንን ጥሬ እቃ በአግባቡ በመጠቀም ሕዝብን እና ሀገርን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን እና ለሚ ናሽናል ሲሚንቶም የተፈጥሮ ሃብትን የመጠቀም አንዱ ማሳያ መኾኑን አንስተዋል።
ሲሚንቶ ፋብሪካው የአካባቢውን ነዋሪዎች በበርካታ ዘርፎች ተጠቃሚ የሚያደርግ በመኾኑ ማኅበረሰቡ ለፋብሪካው ኹነኛ ተንከባካቢ መኾን እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀሪ የፋብሪካው የግንባታ ሥራዎችን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ በትኩረት ይሠራል ብለዋል። ምርት ለማስጀመር የሚያስችሉ ከውጭ የሚገቡ ቁሳቁስ በፍጥነት ወደሀገር እንዲገቡም አስፈላጊው ሥራ ይከናወናል ብለዋል።
ለልማት ተነሽዎች ያልተከፈለ ካሳ ስለመኖሩ በፕሮጀክቱ አመራሮች የተነሳ ሲኾን ይህ የካሳ ክፍያ ጥያቄ በአጭር ጊዜ ተፈጻሚ ለማድረግ እንደሚሠራ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
በአካባቢው የጸጥታ ችግር ተፈጥሮ እንደነበር የጠቆሙት አቶ ተመስገን አሁን ላይ አንጻራዊ ሰላም መስፈኑን ተናግረዋል። የፋብሪካው ግንባታ በሙሉ አቅም እየተከናወነ ነው፣ የሚያሰጋ የጸጥታ ችግርም የለም ብለዋል። ሰላም ወዳዱ ሕዝብ ሰላሙን በማስከበር እና ፋብሪካውን በመንከባከብ አሁን በግንባታ ወቅት እያገኘ ያለውን ጥቅም በምርት ወቅትም በላቀ ሁኔታ ማስቀጠል ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!