“የለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካን በአጭር ጊዜ ወደ ሥራ ለማስገባት በትኩረት እየተሠራ ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

80

ባሕር ዳር: መጋቢት 2/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካን በአጭር ጊዜ ወደ ሥራ ለማስገባት በትኩረት እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ እና ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደን ጨምሮ የፌዴራል እና የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች የለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካን የግንባታ እንቅስቃሴ ተመልክተዋል።

ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በዚህ ወቅት እንዳሉት በፋብሪካው ግንባታ ዙሪያ የሚገጥሙ ችግሮችን ሁሉ በፍጥነት በመፍታት በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ ክልሉ እየሠራ ነው።

ፋብሪካው በአጭር ጊዜ ምርት እንደሚጀምርም ገልጸዋል። ቀልጣፋ የምርት ማጓጓዝ ሂደት እንዲኖር ለማስቻል ከለሚ እስከ ደብረ ብርሃን ያለው መንገድ ደረጃውን ጠብቆ እንደሚገነባ፤ ይህም ሥራ በቅርብ ቀን እንደሚጀመር ርእሰ መሥተዳድሩ ገልጸዋል።

ከካሳ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጉዳዮችንም በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍትሔ እንሰጣለን ብለዋል። ለዚህም ባለሙያዎች ወደቦታው ተሰማርተው የካሳ ሥራውን ያከናውናሉ ነው ያሉት። ፋብሪካው ለክልሉ ብሎም ለሀገር ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ አለው፤ የሲሚንቶን ዋጋ ለማረጋጋትም ሁነኛ መፍትሔ ነው ብለዋል ርእሰ መሥተዳድሩ።

የአካባቢው ማኅበረሰብ እና የክልሉ ሕዝብ መሰል ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በሚፈጥሩት የሥራ እድል እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ተጠቃሚ ለመኾን ሰላሙን እያጸና ፕሮጀክቶቹን መንከባከብ እና መጠበቅ እንዳለበትም ርእሰ መሥተዳድሩ አስገንዝበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነገ በ16ኛ መደበኛ ጉባኤው የተለያዩ ውሳኔዎችን ያሳልፋል፡፡
Next article“ለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ ግንባታ ምርት በመጀመር ሕዝብን ተጠቃሚ ለማድረግ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሷል” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ