
በጎጃም ኮማንድፖስት ስር የሚገኘው ክፍለጦር በሰሜን ጎጃም በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች በመሠማራት የፅንፈኛውን አከርካሪ በመስበር ላይ እንደሚገኝ አስታዉቋል።ክፍለጦሩ ከአማራ ክልል የፀጸጥታ ኀይሎች ጋር በመጣመር የዘራፊውን ቡድን አባላት ደምስሷል፣ ሁለት ተሽከርካሪዎችን በቁጥጥር ስር አውሏል።
የክፍለጦሩ አዛዥ ኮሎኔል ይመር ገበየሁ እንደተናገሩት፣ ጽንፈኛው ዘርፎ ከሚከፋፈልበት ቢኮሎ አባይ ጀምሮ ብራቃት፣ ሪም፣ ገርጨጭ እና አማሪት አካባቢዎች የተወሸቀውን አሸባሪ በመጥረግ ሁለት አምቡላንሶችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ተናግሯል።
ወደ ሸጋይ፣ አምቦ መስክ፣ አጋምላ፣ ዲካን፣ ኬር፣ ኔርድ ጎና፣ ላይ ሻንቃ እና ታች ሻንቃ የተሰማራው ኀይል የጽንፈኛውን ዱካ እግር-በእግር እየተከተለ በማፅዳት ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል።
ሠራዊቱን እና የአማራ የፀጥታ ኀይሎች በየደረሱበት ሁሉ ከሕዝብ ጋር ባደረጉት ውይይት፣ ስለሠራዊቱ የተነገራቸው ፕሮፖጋንዳ ሀሰት መሆኑን እና አብረውት ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የክፍለጦሩ አዛዥ ኮሎኔል ይመር፣ በመርዓዊ እና አካባቢው በጽንፈኛው ላይ እርምጃ ተወስዶ አከርካሪው ከተሰበረ በኋላ በአካባቢው ሰላም ሆኗል ብለዋል። ተዋግቶ ማሸነፍ አቅም የሌላቸው ለሕዝቡ ባዶ ተስፋ ሲሰጡት የነበሩት ጽንፈኛ ቡድኖች የተወሰደው ሕጋዊ እርምጃ ወደ ሕዝብ ያነጣጠረ ለማስመሰል መጣራቸው የሽንፈታቸው ምልክት መሆኑንም አረጋግጠዋል።