
ባሕር ዳር: መጋቢት 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ እና ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደን ጨምሮ የፌዴራል እና የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ግዙፉን የለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ የግንባታ እንቅስቃሴን እየተመለከቱ ነው።
በምልከታው ላይ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ የማዕድን ሚኒስትር ኢንጅነር ሀብታሙ ተገኝ፣ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማት ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተማ እና መሰረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር)፣ የአማራ ክልል ማዕድን ቢሮ ኀላፊ ኃይሌ አበበ እና ሌሎችም የፌዴራል እና የክልል የሥራ ኀላፊዎች ናቸው።
ለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን እንሳሮ ወረዳ በለሚ ከተማ አቅራቢያ እየተገነባ ያለ ፋብሪካ ነው። በኢስት አፍሪካን ሆልዲንግ እና በቻይና ባለሃብቶች በጥምረት የሚገነባው ይህ ፋብሪካ በቅርብ ቀን ተመርቆ ወደ ምርት በመግባት የሀገሪቱን 50 በመቶ የሲሚንቶ ፍላጎት እንደሚሸፍን ይጠበቃል።
ለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ የግንባታ ሥራው ተጠናቅቆ በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ሲገባ በቀን ከ130 ሺህ እስከ 150 ሺህ ኩንታል ሲሚንቶ እንደሚያመርት ተጠቁሟል።
ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ከምልከታቸው በተጨማሪ ከግንባታ ፕሮጀክቱ የሥራ ኀላፊዎች ጋር በመነጋገር የግንባታ ሂደቱን በመገምገም በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቅቆ ወደ ማምረት የሚገባበትን አቅጣጫ እንደሚያስቀምጡም ይጠበቃል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!