
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 2/2016 ዓ.ም (አሚኮ) “ፈተናዎችን በጽናት እና በቁርጠኝነት በመሻገር የሕዝባችንን ዘላቂ ሰላም እና ልማት እናረጋግጣለን” በሚል መሪ መልእክት የምክክር እና የውይይት መድረክ በባሕር ዳር ከተማ ተጀምሯል፡፡ በመድረኩ ከክልል እስከ ወረዳ የሚገኙ ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች ተሳታፊዎች ናቸው፡፡
በምክክር መድረኩ መክፈቻ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ክልሉ ባለፉት ሰባት ወራት ፈታኝ፣ አስቸጋሪ ነገር ግን አስተማሪ የኾነ ውስብስብ ፈተናዎችን ማስተናገዱን አንስተዋል፡፡
በክልሉ ተፈጥሮ የነበረው ዘርፈ ብዙ እና ውስብስብ ችግር ሰብዓዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ፣ ማኅበራዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት አድርሷል ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ከምንም በላይ ደግሞ ለአማራ ሕዝብ ነባር እሴት እና ማንነት የሚመጥን አልነበረም ብለዋል፡፡ በክልሉ ተፈጥሮ የነበረው የኅልውና አደጋ ተቀልብሶ አንጻራዊ ሰላም እንዲሰፍን ዋጋ ለከፈሉ የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የክልሉ የፀጥታ መዋቅርም ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ምሥጋና አቅርበዋል፡፡
የክልሉ ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲጸና በርካታ ሥራዎች ይጠይቁናል ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ የፖለቲካ አመራሩ በቁርጠኝነት እና በልበ ሙሉነት ሊሠራ ይገባል ብለዋል፡፡ ክልሉ ከገጠመው የጸጥታ ችግር በተጨማሪ በበርካታ አካባቢዎች ድርቅ መከሰቱን እና ርብርብ የሚጠይቅ መኾኑን አንስተዋል፡፡
የክልሉ ፈተናዎች ውስጣዊ እና ውጫዊ፤ ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ ናቸው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ “ያሳለፍናቸው የፈተና ጊዜያት ምግባራችን እና ተግባራችንን መቅረጽ አለባቸው” ብለዋል፡፡ በምክክር መድረኩ ያለፉትን ወራት በአግባቡ መገምገም፣ በቀጣይ ሊሠሩ በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ የጋራ ግንዛቤ መያዝ እና ክልሉን ወደ ነበረበት አቋሙ ሙሉ በሙሉ መመለስ ይገባል ብለዋል፡፡
ተወያዮቹ በውይይታቸው ግልጽ የሁኔታ ግምገማ፣ በእውቀት እና በእውነት ላይ ያተኮረ ግምገማ፣ ጽናት እና ቁርጠኝነት፣ ምግባር እና ተግባር ሊጣመሩበት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ የፖለቲካ አመራሩ በጽናት፣ በአንድነት እና በመተጋገዝ ለክልሉ ሁለንተናዊ መሻሻል እንዲተጋም ጠይቀዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!