
ባሕር ዳር: መጋቢት 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች የሚሳተፉበት እና በክልሉ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሚመክር የውይይት መድረክ በባሕር ዳር ከተማ ተጀምሯል፡፡
“ፈተናዎችን በጽናት እና በቁርጠኝነት በመሻገር የሕዝባችንን ዘላቂ ሰላም እና ልማት እናረጋግጣለን” በሚል መሪ መልእክት በተዘጋጀው የምክክር እና የውይይት መድረክ ከክልል እስከ ወረዳ የሚገኙ ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች ተሳታፊዎች ናቸው፡፡
በምክክር መድረኩ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት ያስተላለፉት የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ ያለፉት ወራት ለክልሉ ሕዝብ እና መንግሥት ፈታኝ ጊዜያት ነበሩ ብለዋል፡፡
በክልሉ የተፈጠረው ጽንፈኛ ኀይል የደቀነውን አደጋ የክልሉ መንግሥት ለመቀልበስ የሄደበት ብስለት የተሞላበት መንገድ በበጎነት የሚጠቀስ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ አቶ ይርጋ የተከፈለው ዋጋ ውድ የሚባል ቢኾንም ክልሉን ከብተና መታደግ ተችሏል ነው ያሉት፡፡
በክልሉ ለተፈጠረው መጠነ ሰፊ ቀውስ ችግሮቹ ከውስጥም ከውጭም የሚመነጩ እንደነበሩ አንስተዋል፡፡ አቶ ይርጋ በምክክር መድረኩ ችግሮችን መመርመር፣ ክፍተቶችን መለየት፣ የመፍትሄ ሃሳቦችን ማመንጨት እና የቀጣይ ጊዜ ተግባራትን መንደፍ እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል፡፡
አቶ ይርጋ በመልእክታቸው የፖለቲካ አመራሩ ክልሉ የገጠመውን ውስብስብ ችግር እና ፈተና በሚገባ ማጤን ይኖርበታል ብለዋል፡፡ አንዱ የሌላውን ችግር መረዳት፣ ልምድ መቀያየር፣ መደጋገፍ እና መተጋገዝ ወቅቱ የፈጠረውን ፈተና ለመሻገር ምቹ መደላድል እንደኾነም ነው ያስገነዘቡት፡፡
ጽንፈኝነትን መታገል እና ቆራጥ አቋም መያዝ ከፖለቲካ አመራሩ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል፡፡ አቶ ይርጋ “ሕዝብን ያሳተፈ የሰላም ግንባታ ለማድረግ የምክክር መድረኩ አስፈላጊነት የጎላ ነው” ብለዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!