
ባሕርዳር: መጋቢት 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የባሕር ዳር – ደሴ ሰበካ ሐዋርያዊ ሥራዎች ማስተባበሪያ ቢሮ በባሕር ዳር ከተማ ለሚኖሩ የአካል ጉዳተኞች እና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ወገኖች ማዕድ አጋርቷል። የማነቃቂያ እና የማበረታቻ ንግግርም ተደርጓል።
በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የባሕር ዳር – ደሴ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ልሳነ ክርሥቶስ ማቴዎስ ”ድምቀት” በሚል ስያሜ የተደረገው ማዕድ ማጋራት የተረሱ እና በተሳሳተ ሃሳብ የምናያቸውን ሰዎች እንድናስታውሳቸው በማሰብ መኾኑን ገልጸዋል። የተጎዱ እና አካል ጉዳት ያለባቸውን ወገኖች እንደምንጠቅማቸው እና እንደሚጠቅሙን ለማስታወስም ነው ብለዋል። የክርስቶስ ደስታ ሙሉ እንዲኾን የእርስ በእርስ በተለይም ለችግረኞች ፍቅር የመስጠትን አስፈላጊነት ገልጸዋል።
ችግረኞች እና አካል ጉዳተኞችም የሚያስባቸው ወገን እንዳላቸው የማስገንዘብን አስፈላጊነትን ጠቅሰዋል። አካል ጉዳተኞች በማኅበረሰቡ ውስጥ በምቹ ኹኔታ እንዲኖሩ ማመቻቸት ኀላፊነት አለብን ብለዋል። የሃይማኖት ተቋማት ቢተባበሩ አካል ጉዳተኞች እንደማይከብዷቸው ገልጸዋል።
በቤተ ክርስቲያኗ የባሕር ዳር – ደሴ ሀገረ ስብከት የትምህርት ዴስክ ኀላፊ ወንድም አቦነህ በበኩላቸው የማዕድ ማጋራቱ ዓላማ አሳቢ ያጡ የተገፉ እና የተቸገሩ አካል ጉዳተኞች ለፆም መያዣ የምሳ ግብዣ እና አባታዊ ቡራኬ ለመስጠት ነው ብለዋል። አካል ጉዳተኞች በበዓሉ ደምቀው አብረን ለመዋል ሲሉ ተናግረዋል።
ፕሮግራሙን በማዘጋጀታችን ደስተኞች ነን ያሉት አቶ ወንድም አካል ጉዳተኞች በየሚደርሱበት የሚገጥማቸውን የመገፋት ስሜት አብረን በመዋል አብሮነታችንን ለማሳየት ነውም ብለዋል። በተለይ ፆሙ ሲጀመር አብሮ ለመፆም እና ለመጸለይም መኾኑን ገልጸዋል። የፕሮግራሙ ተሳታፊዎች በየእምነት ቤታቸውም ሲሄዱ አብሮነትን እና መረዳዳትን እንዲሰብኩ እና እንዲያስፋፉ አሳስበዋል።
የአማራ ክልል የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ፍሬሰላም ዘገየ የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ በየትኛውም ተቋማት ተካትቶ የመፈጸሙን አስፈላጊነት ጠቅሰዋል። እስካሁን ያልሠራነው በሃይማኖት ተቋማት ላይ ነበር ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያኗ ለአካል ጉዳተኞች ትኩረት ሰጥታ በመሥራቷ አመሰግናለሁ ብለዋል።
በክልሉ ውስጥ 4 ሚሊዮን የሚኾኑ አካል ጉዳተኞች መኖራቸውን ጠቅሰው ሁሉም የሃይማኖቶች አባል በመኾናቸው እንደ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሌሎቹም መሰል መልካም ሥራዎችን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።
በማዕድ ማጋራቱ የተገኙ እና አስተያየታቸውን ለአሚኮ የሰጡ አካል ጉዳተኛ እና ችግረኛ ወገኖች ቤተክርስቲያኗ የፆም መያዣ የማዕድ ማጋራት በማድረጓ አመስግነዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ የፆመውን ፆም መታሰቢያ ለመፆም በተደረገላቸው የምሳ ግብዣ መደሰታቸውን ገልጸዋል። ሌሎች የሃይማኖት ተቋማትም ለችግረኛ ወገኖች መሰል ሥራ እንዲሠሩ አሳስበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!