
ባሕር ዳር: መጋቢት 1/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የ1 ሺህ 445ኛውን የወርሃ ረመዷን ፆምን አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫው “ረመዷንን የሠላም፣ የፍቅር፣ የመተባበር እና የመተጋገዝ አድርገን መፆም ይገባናል” ሲሉ የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤትፕሬዚዳንት ሺህ ጀውሃር ሙሐመድ አሳሰበዋል።
የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ሽህ ሙሐመድ አንዋር በበኩላቸው “በዚህ ወር የምስኪኖችን፣ የድሆችን እና የጎረቤቶቻችንን ችግር የምንጋራበት እና አይዟችሁ የምንልበት ወር ይኾን ዘንድ አደራ” ብለዋል።
“ታላቁን ረመዷንን ስንፆም ከምግብ እና መጠጥ ራስን ማቀብ ብቻ ሳይኾን ከሐሜት፣ ከስድብ፣ ከመገዳደል እና አላስፈላጊ ከኾኑ ነገሮች ሁሉ ራስን በማቀብ መኾን አለበት” ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ሼህ ዓብዱራህማን ሱልጣን ናቸው።
ዋና ጸሐፊው አያይዘውም በመላው ዓለም ለምትገኙ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች እና የክልላችን ሙስሊሞች እንኳን ለ1 ሺህ 445ኛዉ የወርሃ ረመዷን ፆም አሏህ በስላም አደረሳችሁ አደረሰን ብለዋል፡፡
ስንናፍቀው የኖርነው የጠንካራ ሕዝባዊ አንድነታችን ማሳያ፤ ወደ አምላካችን አላህ መቃረቢያ የኾነው ታላቁ ረመዷን ደጃችን ላይ ደርሷል ነው ያሉት።
በክልሉ በኹሉም ዞኖች የመጅሊስ መዋቅርን አስተካክለን ለዚህ ታሪካዊ ክስተት ለተከበረው የረመዷን ወር በመድረሳችን ለአላህ ምስጋናችንን እናቀርባለን ብለዋል ዋና ጸሐፊው።
መጅሊሳችን ሁሉንም ሙስሊም አቅፎ እና ደግፎ የሚይዝ ነው ያሉት ዋና ጸሐፊው ከቡድን እና ከወገንተኛነት የጸዳ ጠንካራ ተቋም እንዲኾን ኹሉም ሙስሊም ድጋፍ ማድረግ ይገባዋል ብለዋል።
የረመዷን ወርን ስንፆም የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት በተለይ የተፈናቀሉትን እና በመሰል አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ወገኖቻችን በሶደቃ በማሰብ መኾን አለበትም ብለዋል።
ሁሉም የእስልምና እምነት ተከታይ ለሀገራችን እና ለክልላችን ሰላም እንዲሁም ዘላቂ ልማት የሚጠበቅበትን ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።
የክልሉ መንግሥት እና የፀጥታ አካላት የረመዷን ፆም እና ስግደት በሰላም እንዲጠናቀቅም የሚጠበቅባቸውን ኀላፊነት እንዲወጡ ዋና ጸሐፊው አስታውሰዋል።
ዘጋቢ:-ሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!