
ባሕር ዳር: መጋቢት 1/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በክልሉ ወቅታዊ የሰላም፣ የልማት፣ የመልካም አሥተዳደር እና የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ላይ ትኩረት ያደረገ የምክክር መድረክ በባሕር ዳር ይካሄዳል።
የምክክር መድረኩ ዓላማ ባለፉት ሰባት ወራት በጽንፈኛው እና ዘራፊው ኃይል በክልሉ የተፈጠረውን የሰላም እጦት ችግር ለመቀልበስ የተሠራውን የሕግ ማስከበር ሥራ ጨምሮ ጎን ለጎን የተከናወኑ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች ለመገምገም ያለመ ነው ተብሏል።
የምክክር መድረኩን ዓላማ አስመልክቶ በጽሕፈት ቤታቸው መግለጫ የሰጡት በአማራ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር) የምክክር መድረኩ በክልሉ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያለፈውን ገምግሞ ለቀጣዩ አቅጣጫ ያስቀምጣል ብለዋል።
ባለፉት ሰባት ወራት በጽንፈኛ ኃይሎች የተፈጠረውን ቀውስ እና ክልሉ በችግር ውስጥም ሆኖም የተሠሩ የልማት እና መልካም አስተዳደር ስራዎች በጥልቀት እንደሚገመገሙ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር) ተናግረዋል፡፡
የክልሉ ሕዝብ ከሐምሌ አጋማሽ ጀምሮ በጽንፈኛው እና ዘራፊው ኃይል በተፈጠረው ቀውስ ምክንያት ለከፍተኛ ጉዳት ተዳርጎ ቆይቷል ያሉት ዶክተር ዘሪሁን ፍቅሩ ጽንፈኛው ኃይል ዋና ዓላማው በሕዝብ የተመረጠን መንግስት በኃይል በማስወገድ ክልሉን ለማፍረስ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ይህ ጽንፈኛ ኃይል በክልሉ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት አድርሷል ያሉት ዘሪሁን ፍቅር (ዶ.ር) በተለይም በድልድዮች፣ በመብራት ሰብስቴሽኖች ጉዳት አድርሷል፣ በርካታ ተቋማትንም አውድሟል ብለዋል፡፡ በበርካታ የክልላችን አካባቢዎች የሚገኙ መንገዶችን በመዝጋት የምርትና አገልግሎት ዝውውርን በመግታት ሕዝባችንን ለከፋ ጉዳት እንደዳረገም ተናግረዋል፡፡ ይህ የፅንፈኛ ኃይል በክልሉ ያሉ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች እንዲቋረጡ እና እንዲወድሙ ከማድረጉ ባሻገር አርሶ አደሩ የማምረት ስራውን በአግባቡ እንዳያከናውኑ በማድረግ ለከፋ ድህነት እንድንዳረግ እየሠራ ስለመሆኑም አክለው ገልፀዋል፡፡
በድርቅ ተጎጂ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የዕለት እርዳት እንዳይደረስ ከማድረግ ባለፈም የዕርዳታ እህል ዘርፏል ብለዋል፡፡
ክልሉ በጽንፈኛው ቡድን በሕዝብ የተመረጠን ሕጋዊ መንግሥት በኃይል፣ በአመጽ እና ሽብር አስወግዶ ስልጣን ለመቆጣጠር ያለመ የሰላም መደፍረስ ችግር አጋጥሞት ነበር ያሉት ዶክተር ዘሪሁን በሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ በፌዴራል እና በክልሉ የጸጥታ መዋቅር የጋራ ጥምረት ሙከራዎች ከሽፈዋል ብለዋል። በክልሉ የመጣውን አንጻራዊ ሰላም ለማጽናት እና ለማስቀጠል በየደረጃው የሚገኘው አመራር ውይይት እና ምክክር አስፈላጊ መኾኑንም አንስተዋል።
“ክልሉ ከገጠመው ቀውስ በፍጥነት ወጥቶ ሕዝቡ የተረጋጋ ሕይወት እንዲመራ መፍጠር፣ መፍጠን፣ ቅንጀት እና ተግባቦት ያስፈልጋል” ያሉት ዶክተር ዘሪሁን አመራሩ ክልሉ በገጠመው ችግር ዙሪያ ተቀራራቢ አረዳድ እና ግንዛቤ እንዲኖረው የምክክር መድረኩ የጎላ ፋይዳ ይኖረዋል ነው ያሉት።
በክልሉ በተፈጠረው የሰላም መደፍረስ ችግር ከተከሰተው ሰብዓዊ ጉዳት በተጨማሪ መንገድ፣ መብራት፣ ማኅበራዊ ተቋማት፣ የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መዳረሻዎች በጽንፈኛውና ዘራፊው ኀይል ውድመት እና ዘረፋ ተፈጽሞባቸዋል ብለዋል። አርሶ አደሮች መደበኛ የእርሻ ሥራቸውን በወቅቱ እንዳያከናውኑ የአፈር መዳበሪያ እና የግብዓት አቅርቦት ዘረፋ ተፈጽሟል ያሉት የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊው የክልሉ ሕዝብ ያመረተውን ለገበያ እንዳያቀርብ መንገድ ተዘግቶ ዘርፈ ብዙ ጉዳት እንዲደርስበት ተደርጓል ብለዋል።
የምክክር መድረኩ ዓላማም ያለፈውን ጊዜ አፈጻጸም ገምግሞ ለቀሪ ጊዜያት አቅጣጫ ማስቀመጥ ላይ እንደሚያተኩር ተናግረዋል። የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ለማጽናት ሕግ ማስከበር፣ ጠንካራ የሕዝብ ተግባቦት መፍጠር እና ከሰላም ማጽናት ጎን ለጎን የልማት እና መልካም አሥተዳደር ሥራዎችን ለማስቀጠል የጋራ መግባባት ይያዝበታል ተብሎ ይጠበቃል ነው ያሉት።
በምክክር መድረኩ በባለፈው የቀውስ ወራት የባከኑ ሥራዎችን ማካካስ በሚቻልባቸው ነጥቦች ዙሪያ ትኩረት ያደርጋል ተብሎ እንደሚጠበቅም ዶክተር ዘሪሁን ተናግረዋል።
የምክክር መድረኩ ከመጋቢት 2/2016 ዓ.ም እስከ መጋቢት 5/2016 ዓ.ም ለተከታታይ አራት ቀናት የሚቆይ ይኾናል ተብሏል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!