ከአካባቢያዊነት የተሻገረው ሰውነት!

28

ባሕር ዳር: መጋቢት 1/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአንዳንድ ሰዎች መወለድ እንዲህ ነው። ከራስ አልፎ ለቤተሰብ፣ ከቤተሰብ አልፎ ለማኅበረሰብ፣ ከማኅበረሰብ አልፎ ለሀገር፣ ከሀገር ሁሉ አልፈው ዓለም አቀፍ ዜጋ የሚኾኑ አሉ።

ካትሪን ሐምሊን በአውስትራሊያ ሲድኒ ነበር የተወለዱት። ከግማሽ በላይ የሚኾነውን ዕድሜያቸውን ያሳለፉት ለኢትዮጵያ በመሥራት እና ኢትዮጵያን በማስተዋወቅ ነው።

ሐምሊን በሲድኒ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ የልምምድ ቆይታቸውን ቅዱስ ዮሴፍ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ በተባሉ ሆስፒታሎች አጠናቀዋል። ከዚያም ‹‹ክራውን ስትሪት›› ወደተባለው የሴቶች ሆስፒታል ገብተው የሁልጊዜም ምኞታቸው የነበረውን ሴቶችን የመርዳት ተግባራቸውን ጀመሩ። በዚህ ወቅትም ከዶክተር ሬጂናልድ ሐምሊን ጋር ተዋውቀው ለትዳር በቅተዋል። ተግባራቸውን በማስቀጠልም ከአካባቢያቸው እስከ ሀገራቸው አንቱ ያስባሉ ተግባራትን ፈጽመዋል፡፡ የአስተሳሰብ አድማስ ሲሰፋ ከቀየ ወጥቶ ሌላውን ማገልገል የሚል የአስተሳሰብ ልህቀት ላይ ይደረሳል እና ዶክተር ሐምሊንም የአስተሳሰብ አድማሳቸው ሰፍቶ ግልጋሎታቸውን ለዓለም ለማዳረስ ማሰብ ጀመሩ፡፡

ልክ በዚህ ሳምንት በ1951 ዓ.ም ጥንዶቹ ዶክተሮች ህልማቸውን እውን የሚያደርግ የኢትዮጵያ መንግሥት የአዋላጅነት ሙያ ማሰልጠኛ ተቋም ለመክፈት ያለውን ፍላጎት የሚገልጽ ማስታወቂያ ተመለከቱ።

በዚህ ጊዜ ታዲያ ሐምሊን ሪቻርድ ከተባለው የስድስት ዓመት ልጃቸው ጋር ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ተቋሙን የማቋቋም ኀላፊነትን ተረከቡ። ለሦስት ዓመታት ቆይታ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት እነዚህ ጥንዶች እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ በኢትዮጵያ ይቆያሉ ብሎ የገመተ አልነበረም።

ጥንዶቹ ወደ ኢትዮጵያ እንደመጡ ሥራቸውን የጀመሩት በልዕልት ፀሐይ ኃይለሥላሴ መታሰቢያ ሆስፒታል ውስጥ ነበር። በወቅቱ እነካትሪን የተመለከቱት በወሊድ ወቅት በሚከሰት ችግር (ፊስቱላ) ምክንያት የሚሰቃዩ ሴቶች መከራ ፈፅሞ ያልጠበቁት ኾኖባቸው ነበር።

እነርሱ ኢትዮጵያ ከመድረሳቸው በፊት የፊስቱላ ችግር ያለባቸው ሴቶች እንኳን ተገቢውን ሕክምና ማግኘት ይቅርና እንደሰው የሚቆጥራቸው አጥተው የሚደርስባቸው መገለል እጅግ በጣም አስከፊ ነበር።

እንዲህ ዓይነት ስቃይ ከዚህ ቀደም አጋጥሟቸው የማያውቁት ጥንዶቹ ዶክተሮች የራሳቸውን የሕክምና መመሪያ በማዘጋጀት የኢትዮጵያውያኑን ሴቶች ሕይወት የመታደግ ተግባራቸውን ጀመሩ።

ተግባራቸው በሰዎች ዘንድ ሲሰማ በርካታ ሴቶች ለሕክምና መጉረፍ ጀመሩ። በመጀመሪያ ልዕልት ፀሐይ ኃይለሥላሴ መታሰቢያ ሆስፒታል ውስጥ 10 አልጋዎች ያሉት ክሊኒክ አቋቋሙ። በግንቦት 1968 ዓ.ም ደግሞ የአዲስ አበባ ፊስቱላ ሆስፒታልን ከፈቱ።

የዶክተር ካትሪን ሴቶችን የመርዳት ተግባራቸው ሴቶቹን በማከም ላይ ብቻ የተገደበ አልነበረም። አዋላጅ ነርሶችን የማሠልጠን ሕልማቸውን ለማሳካት በ2000 ዓ.ም የሐምሊን አዋላጅ ነርሶች ማሰልጠኛ ኮሌጅ እንዲቋቋም አድርገዋል።

አዋላጅ ነርሶቹ ሥልጠናቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በገጠራማ የኢትዮጵያ ክፍሎች በሚገኙ ክሊኒኮች ተመድበው ያገለግላሉ። የአዲስ አበባ ፊስቱላ ሆስፒታል ከኢትዮጵያውያን በተጨማሪ የፊስቱላ ችግር ተጠቂዎች ካሉባቸው ሀገራት የሚመጡ ሠልጣኞችንም ያስተምራል። ከነዚህም መካከል የኬንያ፣ የኮንጎና የባንግላዴሽ ባለሙያዎች ይጠቀሳሉ።

ሐምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ በመባል የሚታወቀው ማዕከል ስድስት ሆስፒታሎችን “ደስታ መንደር” የተባለ የማገገሚያ ማዕከልን፣ የሐምሊን አዋላጅ ነርሶች ማሠልጠኛ ኮሌጅን እንዲሁም በሐምሊን የሚታገዙ 80 የማዋለጃ ክሊኒኮችን አስተሳስሮ የያዘ ተቋም ኾኗል።

ማዕከሉ ፊስቱላን ከማከም በተጨማሪ ችግሩ እንዳይከሰት አስቀድሞ የመከላከል እና ከችግሩ የተላቀቁ ሴቶች በማኅበረሰቡ ውስጥ ተቀባይነት እንዲኖራቸው እና የበቁ እንዲኾኑ የሚያስችሉ ተግባራትን ያከናውናል።

ሕይወታቸውን ሁሉ ሰዎችን ማዳን የኾኑት እኚህ ሰው ለቁጥር የሚታክቱ ሽልማቶችን ተቀብለዋል፡፡

ከሽልማታቸው ውስጥ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በግንቦት 2011 ዓ.ም የዶክተር ካትሪን ሐምሊን እና የባለቤታቸውን የዶክተር ሬጂናልድ ሐምሊን የመታሰቢያ ሐውልትን በመረቁበት እና ለዶክተር ካትሪን ሐምሊን የሰጡት የወርቅ ሽልማት ይጠቀሳል ይህን ሽልማት ሲያበረክቱ እንዳሉትም “ዶክተር ካትሪን ከእኔ ዘር ውጭ አላይም የሚል አመለካከት በበዛበት በአሁኑ ወቅት ከዘር፣ ከቀለም፣ ከጾታ በላይ ሰውነትን እና ሰውን ማዳን ያሳዩ እናት ናቸው።

ሕዝቡ ከእርሳቸው ተግባር መማር ይገባዋል፤ እኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትም እንደዚህ ዘመን የማይሽረው ለትውልድ የሚጠቅም አሻራ ለማስቀመጥ መሥራት ይጠበቅብናል” ብለው ነበር።

በ60 ዓመታት ወርቃማ የኢትዮጵያ ቆይታቸው ከ60 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ኢትዮጵያውያን ሕይወት የሰጡት አንጋፋዋ የፅንስ እና የማህፀን ስፔሻሊስት ሐኪም ዶክተር ኤሊኖር ካትሪን ሐምሊን በ96 ዓመታቸው መጋቢት 9 ቀን 2012 ዓ.ም ከ60 ዓመታት በላይ በኖሩባት እና ባገለገሏት ኢትዮጵያ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

ምንጭ ፡- ‹‹The Hospital By the River: A Story of Hope›› በሚል ርዕስ የተጻፈው የሕይወት ታሪካቸው፡፡
—————————————-//—————————

የኢትዮጵያዊያን ሌላው የጀግንነት ገጽ!

በዚህ ሳምንት የካቲት 26 ቀን 1970 ዓ.ም ከተፈጠሩ ክስተቶች መካካል የካራማራው ድል አንዱ ነው። ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ከዓድዋ ቀጥሎ ከወራሪ ራሳቸውን የተከላከሉበት እና ነፃነታቸውን ያስጠበቁበት የድል በዓል ነው። በወቅቱ በዚያድ ባሬ ይመራ የነበረው ተስፋፊው የሶማሊያ መንግሥት “ታላቋን ሶማሊያ እገነባለሁ” በሚል ሕልም የኢትዮጵያን መሬት ለመውረር አስቦ እሱም ልክ እንደ ጌቶቹ የአውሮፓውያን ሽንፈትን ተከናንቦ የተመለሰበት ክስተት ነው።

ለወረራ አሰፍስፎ በመጣው የዚያድ ባሬ ጦር ከሐምሌ 1969 ዓ.ም እስከ የካቲት 1970 ዓ.ም ድረስ ምሥራቃዊዋ የኢትዮጵያ ክፍል ኦጋዴን ጦርነት ተካሄደባት። ኢትዮጵያ በወቅቱ እርስ በእርስ ግጭት ውስጥ ኾና የተዳከመች ሲመስለው እቅዱን ለማሳካት ጊዜው አሁን ነው በሚል ህልሙን ለማሳካት ጦር ሰበቀ።

ዚያድ ባሬ ያሰበውን ዳር ለማድረስ የኢትዮጵያን ጠላቶች ተጠቀመ። ያዋጣኛል ያለውን የሴራ መንገድ ሁሉ ተከተለ። ሶማሊያ በ1969 ዓ.ም በኢትዮጵያ ላይ ግልጽ ወረራ ከመፈፀሟ በፊት በህቡዕ በተደራጀ ቡድን ተደጋጋሚ ጥቃት በመሰንዘር የኢትዮጵያን የመከላከያ ኃይል ማዳከም የሴራው አካል ነበር። ጦርነቱ በግልጽ በታወጀበት 1969 ዓ.ም ጀምሮ የሶማሊያ ጦር ባልታሰበ መልኩ ጅግጅጋ፣ ሐረር እና ድሬድዋ ድረስ ዘልቆ ገባ።

በመጀመሪያ በሶቭየት ኅብረት እና በመቀጠልም በአሜሪካ ድጋፍ የነበረው የፕሬዚዳንት ዚያድ ባሬ ጦር ለድል የተቃረበ መሰለ። የኋላ ኋላ የውጭ ድጋፍ እየቀነሰበት የመጣው የሶማሊያ ጦር የኢትዮጵያ የውስጥ ኀይሎች የውስጥ ለውስጥ ድጋፍ ስላልተለየው ጦርነቱን ከመግፋት አልተቆጠበም ነበር። ልክ እንደ ዓድዋው የኢትዮጵያው መሪ ለጀግና ሕዝባቸው የክተት ጥሪ አቀረቡ። ሚያዚያ 4 ቀን 1969 ዓ.ም በብሔራዊ ቴሌቪዥን ቀርበው ኮሎኔል መንግሥቱ ኀይለማርያም የክተት ጥሪ አቀረቡ።

“ታፍራ እና ተከብራ የኖረችው ኢትዮጵያ ተደፍራለች። ለብዙ ሺህ ዓመታት አስከብሮን የኖረው አኩሪ ታሪካችን በዚህ አብዮታዊ አዲስ ትውልድ ጊዜ መጉደፍ የለበትም፤ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ሕዝብ! ለክብርህ እና ለነፃነትህ ስትል ከመለዮ ለባሹ ጋር ተሰልፈህ ወራሪውን ኀይል ለመደምሰስ የምትዘጋጅበት ጊዜ አሁን ነው። ተነስ! ታጠቅ! እናሸንፋለን!” ሲሉ አወጁ፡፡

በተደረገለት ጥሪ የኢትዮጵያ ሕዝብም የአገሩን ዳር ድንበር ለማስከበር ቀፎው እንደተነካ ንብ በቁጣ ወጣ። የኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ጦር ወደ ፍፁሜያዊ ማጥቃት እና እልህ አስጨራሽ ጦርነት መግባቱን የሚያመላክቱ እርምጃዎች መታየት ጀመሩ። ከኦጋዴን ሞቃታማ ቦታዎች በአንዱ “ካራማራ” ከሚባለው ተራራ ከምድርም ከሰማይም እሳት የሚተፉ የኢትዮጵያ ወታደር የጦር አረሮች በምድሪቱ ላይ ዘነበባት። ታላቋን ሶማሊያ የመመሥረት ሕልም አንግቦ የነበረው የዚያድ ባሬ ጦር አይቀጡ ቅጣት ተቀጣ። ኢትዮጵያ በታሪክ እንደለመደችው አሁንም ድል አደረገች። የካቲት 26 ቀን 1970 ዓ.ም የኢትዮጵያ ጦር፣ የእናት ሀገር ወዶ ዘማቾች የዚያድ ባሬን ጦር ድባቅ መትተው የኢትዮጵያን አሸናፊነት ታወጀ።

ምንጭ፡- ከኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም “ትግላችን ቅጽ ፩” መጽሐፍ

“የካራማራ ግራሮች” መቅደስ ዐቢይ በ2014 ከአሳተመችው መጽሐፍ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሴቶች ለሀገር ሰላም እና ልማት ያላቸውን እምቅ አቅም አሟጠው ሊጠቀሙ እንደሚገባ ተገለጸ።
Next article“ሕዝበ ክርስቲያኑ ታላቁን የዓብይ ፆም ስንጻም የተቸገሩ ወገኖቹን በማሰብ እና ያለንን በማካፈል ሊኾን ይገባል” ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ