ሴቶች ለሀገር ሰላም እና ልማት ያላቸውን እምቅ አቅም አሟጠው ሊጠቀሙ እንደሚገባ ተገለጸ።

53

እንጅባራ: የካቲት 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ”ሴቶችን እናብቃ ልማት እና ሰላምን እናረጋግጥ” በሚል መሪ ሃሳብ በእንጅባራ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሮ ውሏል።

በዓለም ዙሪያ ያሉ ሴቶች መብት እና ጥቅሞቻቸውን ለማስከበር ባደረጉት ተጋድሎ ዙሪያ ትኩረቱን አድርጎ ላለፉት 112 ዓመታት ሲከበር የመጣው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ዘንድሮም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ113ኛ ጊዜ በሀገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ48ኛ ጊዜ ተከብሯል። በእንጅባራ ከተማም “የሴቶችን አቅም በማጎልበት ልማት እና ሰላምን ማረጋገጥ ይቻላል” በሚል መሪ ሃሳብ በእንጅባራ ከተማ ተከብሮ ውሏል።

በበዓሉ ሴቶች እና ህፃናትን ከጥቃት እንከላከል፣ በሠላም ግንባታ ሂደት የበኩላችንን ድርሻ እናበርክት፣ ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች እና ህፃናት ድጋፍ እናድርግ የሚሉ ሃሳቦች ተንፀባርቀዋል።

በበዓሉ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ምክትል አሥተዳዳሪ እና የከተማና መሠረተ ልማት መምሪያ ኀላፊ አይተነው ታዴ ሴቶችን ያገለለ ልማትም ኾነ ሰላም ዘላቂነት እንደማይኖረው ገልጸዋል።

ሴቶች ያላቸውን እምቅ አቅም አሟጠው በመጠቀም ለሰላም ግንባታ እና ልማት ሊተጉ እንደሚገባም ምክትል አሥተዳዳሪው አሳስበዋል። የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ሴቶች፣ ህጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ወይዘሮ አምባነሽ ስሜነህ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እና ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለማሳደግ በተሠሩ ሥራዎች የሴቶች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።

ይህም ሴቶች ባለፉት ዓመታት ሁሉን አቀፍ ጥቅሞቻቸውን ለማስከበር ያደረጉት ትግል ፍሬ እያፈራ መኾኑን ማሳያ ነው ብለዋል መምሪያ ኀላፊዋ። በክልሉ ብሎም በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በአሁኑ ወቅት በተፈጠረው የሰላም መደፍረስ ሴቶች እና ህጻናት ቀጥተኛ ተጠቂ ናቸው ያሉት መምሪያ ኀላፊዋ ችግሩን ለመፍታት ሴቶች አወንታዊ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ገልጸዋል። በበዓሉ ማጠቃለያም ለችግር ተጋላጭ ለኾኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች የምግብ እህል እና የቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጓል።

ዘጋቢ:- ሳሙኤል አማረ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሴቶች ሠላምን እያስጠበቁ፣ ሀገር እየገነቡ እና ዘርፈ ብዙ ሚናቸውን እየተወጡ ይገኛሉ” በላይ በዛብህ
Next articleከአካባቢያዊነት የተሻገረው ሰውነት!