“ሴቶች ሠላምን እያስጠበቁ፣ ሀገር እየገነቡ እና ዘርፈ ብዙ ሚናቸውን እየተወጡ ይገኛሉ” በላይ በዛብህ

30

ባሕር ዳር: የካቲት 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የኀብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት “ዓለም አቀፍ የሴቶችን አቅም በማጎልበት የጤና ልማትን እናፋጥን” በሚል መሪ መልዕክት ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን በባሕር ዳር አክብሯል።

የኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ እንዳሉት ሴቶች በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ለፆታዊ ጥቃት እና ለተለያዩ ችግሮች ተጋላጭ የኾኑ የማኀበረሰብ ክፍሎችን የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ ጉልህ ሚና ተጫውተዋል ብለዋል።

ከታሪካችን እንደምንረዳው እነእቴጌ ጣይቱ ሰላምን እያስጠበቁ፣ ሀገር እየገነቡ እና የመሪነት ሚናቸውን በአግባቡ እየተገበሩ የዛሬይቷን ኢትዮጵያ አስረክበውናል ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ። “ሴቶች ሠላምን እያስጠበቁ፣ ሀገር እየገነቡ እና ዘርፈ ብዙ ሚናቸውን እየተወጡ ይገኛሉ” ሲሉም ተናግረዋል።

የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ሴቶች በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ግንባር ድረስ ዘልቀው ሙያዊ እና የዜግነት ግዴታቸውን መወጣታቸውንም ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል። “በሁለንተናዊ ዘርፍ ተጠቃሚ እንድንኾን የኢንስቲትዩቱን ሴቶች በማደራጀት ፎረም አቋቁመን ወደ ሥራ ገብተናል” ብለዋል።

በፎረሙም የሴቶችን የሥራ ፈጣሪነት ሚና በማሳደግ በትምህርት፣ በምጣኔ ሃብት፣ በጤና እና በሌሎችም ጉዳዮች አቅማቸውን በመገንባት ብሎም የውሳኔ ሰጭነት ሚናቸው እንዲጎለብት እየተሠራ መኾኑን አቶ በላይ ጠቁመዋል። ይህም ሴቷ ከፍተኛውን ሥራ እያከናወነች የልፋቷን ባለማግኘቷ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታግላ ያመጣችው ውጤት አንዱ አካል ነው ብለዋል።

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሕክምና ሳይንስ ኮሌጅ የኀብረተሰብ ጤና ትምህርት ቤት ዲን ዓለምፀሐይ መኮንን (ዶ.ር) በበኩላቸው ሴት ልጅ በተሰለፈችበት መስክ ቆራጥ እና የማትችለው ሥራ እንደሌለ አስገንዝበዋል። ሴቶች ወጥተው እንዲሠሩ ወንዶች ማበረታታት ይገባቸዋል ነው ያሉት።

የሥርዓተ ፆታ ባለሙያዋ አሰገደች ተዘራ እንዳሉት በግጭት ወቅት ሕጻናት፣ አካል ጉዳተኞች እና ሴቶች ለከፍ ግጭት የተጋለጡ ናቸው። በመኾኑም ሁሉም ለአንዱ መብት፤ አንዱ ለሁሉም መብት መከበር በመሥራት ዓለም አቀፍ የሴቶችን ቀን የትግል ውጤት በተግባር ማሳየት ይገባናል ብለዋል።
ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በዓለም ለ113ኛ፣ በኢትዮጵያ ለ48ኛ እንዲሁም በክልል ለ29ኛ ጊዜ ተከብሯል።

ዘጋቢ:- ሙሉጌታ ሙጨ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሴቶች ከተለምዷዊ አሠራሮች መውጣት እና ማነቆዎችን በመስበር የማኅበረሰቡ አቅም መኾን ይኖርባቸዋል” የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ
Next articleሴቶች ለሀገር ሰላም እና ልማት ያላቸውን እምቅ አቅም አሟጠው ሊጠቀሙ እንደሚገባ ተገለጸ።