
ባሕር ዳር: የካቲት 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በተከሰተው የጸጥታው ችግር ምክንያት ከ1 ሺህ 500 በላይ የውኃ ተቋማት ላይ ጉዳት መድረሱን የቢሮው ኀላፊ ማማሩ አያሌው (ዶ.ር) ገልጸዋል።
በውኃ ተቋማቱ ላይ የደረሰው ጉዳት ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚገመት ነው የቢሮ ኀላፊው የገለጹት። በደረሰው ውድመት 817 ሺህ የሚኾኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች የንጹህ መጠጥ ውኃ ችግር ውስጥ መውደቃቸውን አንስተዋል።
በዚህ ዓመት ለመገንባት ከታቀዱት 36 የውኃ ተቋማት ውስጥ 21 ፕሮጀክቶች በጸጥታ ችግር ምክንያት ተቋርጠዋል ብለዋል። እንደ ዶክተር ማማሩ አያሌው ገለጻ የተቋረጡት ፕሮጀክቶች 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር የሚገመት የገንዘብ አቅም ነበራቸው ብለዋል።
በ140 ሚሊዮን ብር ውል የተያዘባቸው 9 ጥልቅ የውኃ ጉድጓድ ፕሮጀክቶችም በጸጥታው ችግር ምክንያት መቆማቸውንም ነው ኀላፊው የገለጹት።የፀጥታ ችግሩ በነባር የውኃ ተቋማት ላይ ካደረሰው ጉዳት ባሻገር እተገነቡ የሚገኙ ፕሮጀክቶች በመጓተታቸው የንፁህ መጠጥ ውኃ ተጠቃሚ መኾን የሚችለው የሕብረተሰብ ክፍል ይበልጥ ችግር ላይ እንዲወድቅ አድርጓል ብለዋል።
አሁን ላይ አንጻራዊ ሰላም ባለባቸው አካባቢዎች ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ተቋማት በመለየት የጥገና ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል። ማኅበረሰቡ በሰላም እጦቱ እየደረሰ ያለውን ዘርፈ ብዙ ችግር በመረዳት የሰላሙ ባለቤት ሊኾን ይገባል ያሉት ቢሮ ኀላፊው በቀጣይም ሰላም በሰፈነባቸው አካባቢዎች ቅድሚያ በመስጠት የጥገና ሥራው የሚቀጥል ይኾናል ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!