
ባሕር ዳር: የካቲት 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የጎጃም ኮማንድፖስት ትናንት በምዕራብ ጎጃም ዞን ቁጭ አካባቢ ባደረገው ሰላምን የማስከበር ሥራ ከተማረኩት የጽንፈኛው አባላት መካከል የሕዝብዓለም አባዋ እና ቴዲ መኩሪያው ይገኙበታል፡፡
ምርኮኞቹ ከጽንፈኛው ጋር ከተቀላቀሉበት ጊዜ አንስቶ የማገት፣ የመግደል እና ተቋም የማፈራረስ ተግባር ላይ ሲሳተፉ ቆይተዋል። ምርኮኛ የሕዝብዓለም አባዋ በዋድ፣ በቁጭ እና በሌሎች ቦታዎች ላይ ከጽንፈኛው ጋር ተሰልፎ ጥቃት ሲያደርስ መቆየቱን ተናግሯል።
ሌላው ምርኮኛ ቴዲ መኩሪያው በገዳም ዛቡር ቀልቻ ቀበሌ እንደነበር ጠቅሶ የጽንፈኛው ቡድን ያመረተውን እህል እና ገንዘብ ዘርፎ ከመስከረም ወር ጀምሮ አባሉ ካደረገው በኋላ በዋድ እና በተለያዩ ቦታዎች ሲንቀሳቀስ ከርሞ ቁጭ ላይ መማረኩን አስረድቷል ።
ምርኮኞቹ እንደተናገሩት ጽንፈኛው ቡድን ዘር ከማጥፋት፣ ሰው ከመግደል፣ ተሽከርካሪ ከመዝረፍ እና ተቋም ከማፈራረስ ውጭ ለጎጃም ሕዝብ እንዳልጠቀመው ተናግረዋል።
ምርኮኞቹ በሠራዊቱ ቁጥጥር ስር ከዋሉ አንስቶ ሠራዊቱ ሰብዓዊ ክብራቸውን ጠብቆ፣ ምግብ እና ውኃ ስላቀረበላቸው እና እንክብካቤ ስላደረገላቸው አመሥግነዋል፡፡ እውነተኛ የሕዝብ ልጅ መኾኑንም በተግባር እያሳየ መኾኑን ስለመመልከታቸው አረጋግጠዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!