
ጎንደር: የካቲት 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ)
ጎንደር እና አካባቢው ሰፊ ምርት ያለበት ቢሆንም ያልተገባ የንግድ ሰንሰለት መኖሩ የኑሮ ውድነቱ እንዲባባስ እንዳደረገው አስተያየታቸውን የሰጡን የከተማዋ ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ነዋሪዎቹ የኑሮ ውድነቱ ከዕለት ዕለት እየጨመረ መምጣቱ ማኅበረሰቡን እንዲማረር አድርጎታል ብለዋል።
አማራ ሚዳያ ኮርፖሬሽን በጎንደር አራዳ ገበያ ተገኝቶ ለመታዘብ እንደሞከረው ነጭ ሽንኩርት በእስር ከአርሶ አደሩ በ30 ብር ሲሸጥ ነጋዴው ደግሞ ከ80 እሰከ 100 ብር እንደሚሸጥ ታዝቧል። ይህ ሁሉ ልዩነት የመጣው ስግብግብ ነጋዴዎች በመበራከታቸው ነው ሲሉ ሸማቾች አስረድተዋል። አርሶ አደሩን እና ሸማቹን በቀጥታ የማገናኘት እና ሁለቱም ተጠቃሚ የሚሆኑበትን መንገድ መፍጠር ከመንግሥት የሚጠበቅ ተግባር እንደሆነም አመላክተዋል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ ቴዎድሮስ ጸጋዬ የኑሮ ውደነቱን ለማረጋጋት እንደ ከተማ 20 ሚሊዮን ብር በመመደብ ሲሠራ መቆየቱን አንስተዋል። ከ4 ሺህ 500 በላይ ኩንታል የጤፍ እና ሌሎች ምርቶች ለመንግሥት ሠራተኞች እና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች እንደተሰራጨ ገልጸዋል።
አርሶ አደሩን እና ሸማቹን የማገናኘት ሥራ በቅርቡ እንደሚጀመር የገለጹት አቶ ቴዎድሮስ በከተማዋ ሦስት የተመረጡ የገበያ መዳረሻ ቦታዎች ላይ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶች ይቀርባሉ ብለዋል።
አርሶ አደሩ ምርቱን ተሸጠልኝ አልተሸጠልኝ በሚል እሳቤ ውስጥ መግባት የለበትም ያሉት አቶ ቴዎድሮስ በሚዘጋጁ የገበያ መዳረሻዎች ላይ መጋዘን ወይም ሸዶች ይዘጋጃሉ ብለዋል።
የኑሮ ውድነቱ ለማረጋጋት የሁሉንም አካል ርብርብ እንደሚጠይቅ ገልጸዋል።
ዘጋቢ: ደስታ ካሣ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!