“967 የጤና ተቋማት በጽንፈኛው ቡድን ተዘርፈዋል” የአማራ ክልል ጤና ቢሮ

84

ባሕር ዳር: የካቲት 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ አብዱል ከሪም መንግሥቱ በክልሉ የተፈጠረው የፀጥታ መደፍረስ በክልሉ የጤና አገልግሎት ላይ ያስከተለውን ችግር አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።

የክልሉን ሕዝብ ጥያቄ እናስመልሳለን በሚል ሰበብ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላት የክልሉን ሕዝብ የጤና መሠረተ ልማት አውድመዋል፤ መድኃኒቶችን ዘርፈዋል፤ አንቡላንሶችንም ነጥቀዋል ሲሉ በመግለጫቸው አመላክተዋል።

በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት አንቡላንሶች ለእናቶች፣ ለሕጻናት እና ለተጎጅ ሰዎች እንደሚውሉ ቢታወቅም በክልሉ በአጠቃላይ 124 አንቡላንሶች ከአሽከርካሪዎች እጅ ላይ በታጣቂዎች ተነጥቀው ለግጭት ዓላማ እየዋሉ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

አቶ አብዱልከሪም የፀጥታ ችግሩ በእናቶች ጤና አገልግሎት ላይ ጫና ማሳደሩንም ተናግረዋል። የጤና ክትትል ማድረግ ከነበረባቸው ነፍሰ ጡር እናቶች ውስጥ 36 በመቶ የሚኾኑት ከክትትል ውጭ ናቸው ብለዋል።

በጤና ተቋማት ውስጥ መውለድ ካለባቸው እናቶች ውስጥም 44 በመቶ የሚኾኑ ለአደጋ በሚያጋልጥ መልኩ በቤት ውስጥ እንዲወልዱ ተገድደዋል ነው ያሉት። ይህም በእናቶች ላይ ዘርፈ ብዙ የጤና ምስቅልቅል እያስከተለ ስለመኾኑ በመግለጫቸው አመላክተዋል።

ግጭቱ በሕጻናት ጤና ላይም አደጋ መደቀኑን አንስተዋል። እንደ ቢሮ ኀላፊው ገለጻ በክልሉ 14 በመቶ የሚኾኑ ሕጻናት የጀመሩትን ተከታታይ ክትባት እንዲያቋርጡ ተደርገዋል። ይህም የሕጻናትን እና የጨቅላ ሕጻናትን ጤና በእጅጉ የሚጎዳ ስለመኾኑ አመላክተዋል።

ከ3 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የሕክምና ቁሳቁሶችን በክልሉ በማሰራጨት የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ታልሞ እየተሠራ እንደነበርም ቢሮ ኀላፊው ጠቁመዋል። ይሁን እንጅ መድኃኒቶችን በሚጓጓዙበት ጊዜ መኪኖች እየታገቱ፣ መድኃኒት እና የሕክምና ቁሳቁሶችም እየተዘረፉ ነው ብለዋል። ለአብነትም በሁለት ተሳቢ መኪኖች ሲጓዝ የነበረ “ፕላንፕሌት” የሚባል ለተጎዱ ሕጻናት ብቻ የሚውል አልሚ ምግብ ተዘርፏል ነው ያሉት፡፡

አቶ አብዱልከሪም ማኅበረሰቡ በአቅሙ ከፍሎ እንደ ሕመሙ ልክ እንዲታከም የሚያስችል የጤና መድህን አገልግሎት እንዲያገኝ ጤና ቢሮው በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ይሁን እንጅ የተፈጠረው የፀጥታ ችግር አዳዲስ የጤና መድህን አባላትን ለመመዝገብ እና የነባር አባላትን መረጃ ለማደራጀት እንቅፋት ኾኗል ብለዋል። ማኅበረሰቡ ሕመም ሲገጥመው ወደ ጤና ተቋማት ሔዶ እንዳይታከም መንገድ እየተዘጋበት ችግር ላይ እየወደቀ ስለመኾኑም በመግለጫቸው ጠቁመዋል።

አጠቃላይ በጤና ተቋማት ላይ የደረሰውን ጉዳት በመግለጫቸው ያነሱት ቢሮ ኀላፊው የመድኃኒት ዝርፊያ፣ የጤና መሠረተ ልማት ውድመት እና ኮምፒውተሮች በመዘረፋቸው የጤና መረጃ መጥፋት ገጥሟል ብለዋል። “967 የጤና ተቋማት በጽንፈኛው ቡድን ተዘርፈዋል” ብለዋል ቢሮ ኀላፊው። ይህም በገንዘብ ሲሰላ ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ አላስፈላጊ ዋጋ አስከፍሏል ነው ያሉት።

የጉዳቱን መጠን ለፌዴራል እና ለክልሉ መንግሥት እንዲሁም ለአጋር አካላት በውል በማሳወቅ ጉዳቱን በፍጥነት መልሶ ለመተካት እና የሕዝቡን ጤና ለመጠበቅ ርብርብ እየተደረገ ስለመኾኑም ተናግረዋል። ግጭት በሀገር ላይ ከሚያስከትለው ውድቀት በተጨማሪ የማኅበረሰቡን ጤና በእጅጉ የሚጎዳ ስለመኾኑም አቶ አብዱልከሪም ተናግረዋል። በመኾኑም ግጭት ጠንሳሽ የኾኑ አካላት ለሕዝብ ደህንነት ማሰብ፣ ሰላማዊ ንግግሮችን መከተል፣ አውዳሚ አካሄዶችን ደግሞ መተው አለባቸው ሲሉ አሳስበዋል።

በየአካባቢው የሚገኘው ሕዝብ የጤና ተቋማቶቹን መዘረፍ እና መውደም፣ የልጆቹን ክትባት መቋረጥ እና የነፍሰጡር እናቶችን እንግልት ነጋሪ ሳይሻው በዓይኑ እየተመለከተ ነው ብለዋል። የጤና እክል የገጠማቸው ሰዎች ከቦታ ቦታ ተዘዋውረው እንዳይታከሙ መንገድ እየተዘጋባቸው ስለመኾኑም ሕዝቡ በየዕለቱ የሚታዘበው ሀቅ ነው ብለዋል። ይህ ድርጊት ክልሉን እና ሕዝቡን ወደባሰ ውስብስብ ችግር የሚያስገባ ተግባር መኾኑንም ጠቁመዋል።

በየአካባቢው የሚኖረው ሕዝብ ግጭት ጠንሳሽ አካላትን “በቃ” ሊላቸው እንደሚገባም አሳስበዋል። ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላትንም ሕዝብን ከመበደል ወጥተው በውይይት እና በንግግር ማመን አለባቸው ሲሉ ቢሮ ኀላፊው አስገንዝበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሴቶች በሰላም እጦት ቀዳሚ ሰለባ በመኾናቸው ለሰላም ቅድሚ ሊሰጡ ይገባል” ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ
Next articleሸማቹን እና አርሶ አደሩን በማገናኘት ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ የመጣውን የኑሮ ውድነት ማረጋጋት እንደሚቻል የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።