“ሴቶች በሰላም እጦት ቀዳሚ ሰለባ በመኾናቸው ለሰላም ቅድሚ ሊሰጡ ይገባል” ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

42

አዲስ አበባ: የካቲት 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ሴቶችን እናብቃ፣ ልማት እና ሰላምን እናረጋግጥ በሚል መሪ መልእክት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ113ኛ፣ በኢትዮጵያ ለ48ኛ ጊዜ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን እየተከበረ ይገኛል።

ምንም እንኳን የሴቶች ውክልና አሁን ላይ 45 በመቶ ማድረስ ቢቻልም የሴቶችን እኩል ተጠቃሚነት የማረጋገጡ ጉዳይ አሁንም ብርቱ ጥረት እና ትግል የሚጠይቅ ነው።

የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ሴቶች ማኅበራዊ አገልግሎት የሚያገኙበት እና በሁሉም መስክ ተጠቃሚ የሚኾኑበት እድል አሁንም ክፍተት ይታይበታል ብለዋል። ከንቲባ አዳነች የሴቶች ተሃድሶ እና የልህቀት ማዕከል ተገንብቶ በቅርቡ አገልግሎት እንደሚጀምርም ገልጸዋል። ሴቶችን ማብቃት፣ እኩልነታቸውን ማረጋገጥ፣ ከተለያዩ ጥቃቶች መጠበቅ እንዲሁም እንደሚችሉ ማሳየት አሁን ላይ ካሉ መሪዎች ይጠበቃል ነው ያሉት።

የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ.ር) ቀኑን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልእክት ዛሬ እዚህ ለመድረስ ለቀደምት ፋና ወጊ እናቶች ክብር ይገባል ብለዋል። ሴቶች 50 በመቶውን የሕዝብ ቁጥር እንደሚወክሉም ተናግረዋል፡፡

በዓሉ ሲከበር ሴቶችን በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች እንቅስቃሴ ያደረጉ፣ ተጠቃሚ መኾን ያልቻሉ እና ለጉዳት የተጋለጡትን እያሰቡ እና እየረዱ ሊኾን ይገባል ነው ያሉት። ሴቶችን በልዩ ልዩ መስኮች ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ እና ንቅናቄ በማድረግ ተጠቃሚ እንዲኾኑ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።

2 ሚሊዮን የሚኾኑ ሴቶች በበጎፈቃድ አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ ትችሏል እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ። የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ “እኔን ጨምሮ አሁን ላይ ያለን ሴት መሪዎች እዚህ መድረሳችን ለሴቶች እኩልነት እና ተሰሚነት የተደረገው ትግል ውጤት ነው ብለዋል። ይህም አስመስክረን እንጂ በችሮታ አይደለም” ብለዋል፡፡

ፍትሕ፣ እኩልነት እና ዲሞክራሲ ተረጋገጠ የሚባለው ሴቶች ወደ መሪነት መምጣት ሲችሉ እንደኾነ ፕሬዚዳንቷ ተናግረዋል። ሴቶችን ማብቃት ይገባል ያሉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ በተለይ ሴቶች ትምህርት እንዲያገኙ መደረግ እንዳለበት አብራርተዋል፡፡

የዘንድሮው የአፍረካ ኅብረት አጀንዳ ትምህርት ላይ መኾኑም ተገቢ ነበር ይህንን ኢትዮጵያ ተግባራዊ ልታደርግ ይገባልም ብለዋል። በጾታ ላይ የሚደርስ ጥቃትን መታገል ግድ እንደሚልም ተናግረዋል። የአፍሪካ ሴቶች አመራር ጥምረትን በኢትዮጵያ ማጠናከር ይገባናልም ብለዋል።

ይህ ሁሉ መኾን የሚችለው ሰላም ሲኾን ነው ያሉት ፕሬዚዳንቷ ሰላም ሲጠፋ ሰለባ የሚኾኑት ሴቶች በመኾናቸው ሰላምን ማምጣት እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡ በበዓሉ ላይ የዩኒሴፍ፣ ዩኤን ኤፍ ፒ ኤና ዩኤን ውሜን የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች ተገኝተው መልእክት አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ፡- ድልነሳ መንግሥቴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በክልሉ ሰፊ የመንገድ መሠረተ ልማት እቅድ ቢኖርም ጽንፈኛው ቡድን ሥራው በወቅቱ እንዳይጠናቀቅ አድርጎታል” ጋሻው አወቀ (ዶ.ር)
Next article“967 የጤና ተቋማት በጽንፈኛው ቡድን ተዘርፈዋል” የአማራ ክልል ጤና ቢሮ