“በክልሉ ሰፊ የመንገድ መሠረተ ልማት እቅድ ቢኖርም ጽንፈኛው ቡድን ሥራው በወቅቱ እንዳይጠናቀቅ አድርጎታል” ጋሻው አወቀ (ዶ.ር)

59

ባሕር ዳር: የካቲት 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ በወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

መግለጫውን የሠጡት የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ ኃላፊ ጋሻው አወቀ በአማራ ክልል የመንገድ መሠረተ ልማትን ተደራሽ ለማድረግ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑን አንስተዋል፡፡ እነዚህ የመንገድ መሠረተ ልማቶች ግን በጽንፈኛው ኃይል መስተጓጎል እየደረሰባቸው መኾኑን ተናግዋል፡፡

የመንገድ መሰረተ ልማት ለክልል ሕዝብ ኑሮ መሻሻል፣ እድገት እና መለወጥ ፋይዳው ከፍተኛ ቢኾንም በክልሉ በተከሰተው አለመረጋጋት በሚፈለገው ልክ እየተገነቡ አለመኾናቸውንም ጠቁመዋል፡፡

በአማራ ክልል በተያዘው በጀት ዓመት 579 የመንገድ፣ የድልድይ እና የጥገና ፕሮጀክቶች አሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 518 ፕሮጀክቶች በዚህ ዓመት በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ተጠናቅቀው አገልግሎት ለመሥጠት ወደ ሥራ መግባታቸውንም ጠቁመዋል፡፡

ቢሮው ከእነዚህ የመንገድ ፕሮጀክቶች ውስጥ 90 በመቶ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግም አቅዶ እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ በአጠቃላይ 2 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ከመንግሥት፣ 812 ሚሊዮን ብር ከኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር፣ 800 ሚሊዮን ብር ከኅብረተሰቡ ተሰብስቦ እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡ በእነዚህ ፕሮጀክቶች በድምሩ 3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር የማንቀሳቀስ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

በአማራ ክልል 3 ሺህ 552 ቀበሌዎች አሉ እስካሁን በተሠራ ሥራ 2 ሺህ 696 ቀበሌዎች በመንገድ መሠረተ ልማት ተገናኝተዋል ያሉት ዶክተር ጋሻው፤ በዚህ ዓመት 27 ቀበሌዎችን ቀበሌ ከቀበሌ በሚያገናኝ መንገድ ለማገናኘት እየሠራን ነው ብለዋል፡፡ በዚህም 372 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ በአዲስ ይሠራል፤ 12 ሺህ 239 ኪሎ ሜትር መንገድ ይጠገናል፤ 93 የተለያየ ስትራክቸር ያላቸው ድልድዮችን ለመገንባት መታቀዱን ጠቅሰዋል፡፡

እስካሁንም 172 ከሎ ሜትር ጠጠር መንገድ፣ 4 ሺህ 432 ኪሎ ሜትር የመንገድ ጥገና እና 24 ተንጠልጣይ ድልድዮች እየተሠሩ መኾናቸውን ጠቁመዋል፡፡ ከ18 በላይ ኮንክሪት ድልድዮችም በግንባታ ላይ መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡ በገጠር መንገድ ኤጀንሲም 25 ድልድዮች እየተሠሩ መኾኑን ጠቁመዋል፡፡ የመከላከያ ሠራዊት፣ የክልሉ የጸጥታ ኃይል፣ ተቋራጮች፣ ግለሠቦች እና የአካባቢው ማኅበረሰብ ባደረጉት ድጋፍ በአንጻራዊ ሰላም ውስጥ እየተሠሩ መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡

በአጠቃላይ 53 የድልድይ ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ ገብተዋል ያሉት ኃላፊው 10 ድልድዮች በቅርቡ ተመርቀው አገልግሎት ክፍት ይኾናሉ ነው ያሉት፡፡ ለዚህም ሥራ ማኅበረሰቡ 433 ሚሊዮን ብር አዋጥቷል፤ በ1 ሺህ 943 ኪሎ ሜትር የመንገድ ግንባታ ሥራ ላይም ቀጥታ የጉልበት ድጋፍ አድርጓል ነው ያሉት፡፡

መንገድ የዜጎችን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ በላይ ነው ያሉት ዶክተር ጋሻው የሥራ እድል እንዲፈጠርም የድርሻውን ተወጥቷል ብለዋል፡፡ እስካሁንም ለ5 ሺህ 575 በላይ ወጣቶች የሥራ እድል ፈጥሯል ነው ያሉት፡፡ በስምንት ወር ሊፈጠር ከታቀደው የሥራ እድል ፈጠራም 26 በመቶ መከናወኑን ነው የገለጹት፡፡

በአጠቃላይ እስካሁን 161 ኪሎ ሜትር መንገድ በአዲስ፣ 4 ሺህ 543 ኪሎ ሜትር መንገድ ጥገና እና 53 የተለያዬ ስትራክቸር ያላቸው ድልድዮች እየተገነቡ ነው ብለዋል፡፡ መንገዶችን እና ድልድዮችን በአዲስ ስንገነባ እና ስንጠግን ከፍተኛ ውድመት እና ዘረፋ ተፈጽሞብናል ነው ያሉት ኃላፊው፡፡ በፈተናም ውስጥ ኾነን ግን እየሠራን ነው ብለዋል፡፡

ዶክተር ጋሻው የተከሰተው የሰላም እጦት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ እንዳይጠናቀቁ ከማድረጉም በላይ የገንዘብ እጥረት እንዲፈጠር፣ የሥራ መሥተጓል እንዲከሰት፣ ሕዝቡ ለእንግልት እንዲዳረግ እያደረገ መኾኑን ጠቁመዋል፡፡ ማሽነሪ፣ ተሸከርካሪ፣ ነዳጅ፣ የግንባታ እቃዎች ዝርፊያ እንዲኹም የሠዎች እገታ እየተፈጸመ መኾኑን ጠቁመዋል፡፡

“የመንገድ መሠረተ ልማት ግንባታ የዜጎችን ኢኮኖሚ ከማሳደግ እና ፍትሐዊነትን ከማረጋገጥ በላይ ነው” ያሉት ዶክተር ጋሻው “በምንሠራው ፕሮጀክት ዘረፋ እየተፈጸመበት ነው” ብለዋል፡፡

በክልሉ ሰፊ የመሠረተ ልማት እቅድ ቢኖርም በክልሉ የሚንቀሳቀሰው ጽንፈኛ ቡድን ሥራው በወቅቱ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት እንዳይኾን አድርጎታል ነው ያሉት፡፡ 18 የገጠር መንገድ ፕሮጀክቶች 5 ነጥብ 1 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡ ሎደሮች፣ ስካቫተሮች፣ የሠርቪስ መኪና እና ሲኖትራክ ተዘርፈዋል ነው ያሉት፡፡

በመጨረሻም የመከላከያ ሠራዊት፣ የክልሉ የጸጥታ ኃይል እና ማኅበረሰቡ ሰላም እንዲመጣ እያደረጉት ላለው አስተዋጽኦ ምሥጋናቸውንም አቅርበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ጽንፈኛው ቡድን የፈጠረው ቀውስ በአማራ ክልል ኢንቨስትመንት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል” አቶ እንድሪስ አብዱ
Next article“ሴቶች በሰላም እጦት ቀዳሚ ሰለባ በመኾናቸው ለሰላም ቅድሚ ሊሰጡ ይገባል” ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ