“ጽንፈኛው ቡድን የፈጠረው ቀውስ በአማራ ክልል ኢንቨስትመንት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል” አቶ እንድሪስ አብዱ

61

ባሕር ዳር፡ የካቲት 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ካለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ጀምሮ በክልሉ በርካታ አካባቢዎች የተፈጠረው የሰላም እጦት ከጎዳቸው ምጣኔ ሃብታዊ ዘርፎች መካከል የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ዘርፉ አንዱ ነው፡፡

በክልሉ ስምንት አምራች ኢንዱስትሪዎች እና በርካታ የአበባ፣ አትክልት እና ፍራፍሬ ፕሮጀክቶች በጽንፈኛው ቡድን ውድመት እንደደረሰባቸው የክልሉ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኀላፊ እንድሪስ አብዱ ገልጸዋል፡፡

በክልሉ በተፈጠረው የሰላም እጦት ምክንያት በኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ዘርፉ የደረሰውን ጉዳት በሚመለከት በቢሯቸው መግለጫ የሰጡት አቶ እንድሪስ አብዱ በበጀት ዓመቱ 6 ሺህ 535 አዳዲስ ኢንቨስተሮችን ለመሳብ ታቅዶ በግማሽ ዓመቱ 1 ሺህ 282 ኢንቨስተሮች ብቻ መጥተዋል ብለዋል፡፡ ከእቅዱ አንጻር አፈጻጸሙ ከግማሽ በታች የተመዘገበ ነው ብለዋል፡፡

አዳዲስ ኢንቨስተሮች የገቡባቸው አካባቢዎች አንጻራዊ ሰላም ያለባቸው ብቻ ሳይኾኑ ችግሮች ቢነሱ እንኳን የአካባቢው ማኅበረሰብ የተቋማቱን ደኅንነት የመጠበቅ ልምድ ያለው በመኾኑ ነው ብለዋል፡፡ በአዲስ የገቡት ኢንቨስተሮች ከ176 ቢሊዮን ብር በላይ ኢንቨስት ማድረጋቸውንም ኀላፊው ጠቁመዋል፡፡

በክልሉ የተፈጠረው የሰላም እጦት በአምራች ኢንዱስትሪው ላይ መጠነ ሰፊ ጉዳት አድርሷል ያሉት አቶ እንድሪስ፤ በበጀት ዓመቱ 42 ኢንዱስትሪዎች ምርታቸውን ወደ ውጭ ይልካሉ ተብሎ ቢጠበቅም እስካሁን የላኩት ግን ከ19 አይበልጡም ተብሏል፡፡ ተኪ ምርቶች ላይም አፈጻጸሙ ዝቅተኛ የሚባል መኾኑን ተናግረዋል፡፡

የክልሉ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ከማምረት ጎን ለጎን የሥራ እድል ፈጠራ ላይ ትኩረት አድርጎ ለመሥራት አቅዶ ነበር ያሉት አቶ እንድሪስ ጽንፈኞቹ በፈጠሩት የሰላም እጦት ምክንያት የተፈለገውን ያክል ለውጥ መምጣት አልቻለም ብለዋል፡፡ በበጀት ዓመቱ 61 ሺህ ለኾኑ ወጣቶች የሥራ እድል ለመፍጠር ቢታቀድም የሥራ እድል የተፈጠረላቸው ግን 8 ሺህ 945 ብቻ ናቸው ተብሏል፡፡

“ኢንዱስትሪ ምቾት ይፈልጋል፤ ሰላም ካጣ ምቾትን ፍለጋ ከቦታ ቦታ ይሸጋገራል” ያሉት አቶ እንድሪስ አብዱ በተፈጠረው የሰላም እጦት ምክንያት 6 ሺህ 318 ቋሚ ሠራተኞች ከሥራ ውጭ ኾነዋል ብለዋል፡፡ ችግሩ ምጣኔ ሀብታዊ፣ ማኅበራዊ እና ሥነ ልቦናዊ ቀውስ መፍጠሩንም አቶ እንድሪስ ጠቁመዋል፡፡

አቶ እንድሪስ በመግለጫቸው በክልሉ የተፈጠረውን ቀውስ ተከትሎ በክልሉ የኢንቨስትመንት ፍሰት ቀንሷል፣ የኢንዱስትሪ ምርቶች እንቅስቃሴ ተገትቷል፣ በፕሮጀክቶች ላይ ዘረፋ እና ውድመት ተፈጽሟል ብለዋል፡፡ የክልሉ ሕዝብ ጽንፈኞች እና ዘራፊዎች በሕዝብ ፕሮጀክቶች እና የምጣኔ ሀብታዊ ተቋማት ላይ የሚፈጽሙትን ዘረፋ ግንባር ቀደም ኾኖ ሊከላከል እና ሰላሙን ሊያረጋግጥ ይገባል ነው ያሉት፡፡

በክልሉ አሁን ላይ ያለው አንጻራዊ ሰላም ሙሉ በሙሉ ሲረጋገጥ በበጀት ዓመቱ የእቅድ አፈጻጸም ላይ የነበሩ ውስንነቶችን ለመሙላት በሚያስችል መልኩ ይሠራል ብለዋል፡፡ በቅርቡም በደብረ ብርሃን ከተማ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ መጀመሩን የገለጹት አቶ እንድሪስ ፤ በቀጣይም በሌሎች አካባቢዎች ለማስፋት ይሠራል ብለዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከ8 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የባቡር ሀዲድ ብረት የዘረፋ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የከሚሴ ከተማ አሥተዳደር ፖሊስ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
Next article“በክልሉ ሰፊ የመንገድ መሠረተ ልማት እቅድ ቢኖርም ጽንፈኛው ቡድን ሥራው በወቅቱ እንዳይጠናቀቅ አድርጎታል” ጋሻው አወቀ (ዶ.ር)