
ባሕርዳር: የካቲት 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ፖሊስ ጽሕፈት ቤት የታክቲክ ወንጀል ምርመራ ክፍል ኀላፊ ረዳት ኢንስፔክተር አብዱ ሰይድ እንደገለጹት ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የባቡር ሀዲድ ብረቶችን የዘረፋ ግለሰቦች በኅብረተሰቡ ጥቆማ በቁጥጥር ሥር ማዋል ተችሏል፡፡
ረዳት ኢንስፔክተር አብዱ የባቡር ሀዲድ ብረቶቹ በከሚሴ ከተማ በመኖሪያ ቤት ውስጥ ለመሸጥ ተከማችተው ስለመያዛቸው ነው ያስረዱት፡፡መንግሥት ከፍተኛ ወጭ የሚያደርግበትን እና ለኅብረተሰቡ ከፍተኛ ጥቅም የሚሰጡ ሀብቶችን መጠበቅ ከሁሉም እንደሚጠበቅ አስገንዝበዋል፡፡
ኅብረተሰቡ አገልግሎት የሚሰጡ መሰረተ ልማቶችን በማፍረስ ለግል ጥቅም የሚያውሉ ወንጀለኞችን አጋልጦ እንዲሰጥ እና ድርጊቱ ሲፈጸም ሲያይ ጥቆማ እንዲሰጥም ጠይቀዋል፡፡
የብሔረሰብ አሥተዳደሩ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ እንደዘገበው ረዳት ኢንስፔክተር አብዱ ለአርሶ አደር የሚሰራጭ 8 ኩንታል ማዳበሪያም በቤቱ ውስጥ በቁጥጥር ስር መዋሉን ገልጸዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!