
ደሴ: የካቲት 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሸዋጋ እሸቱ፣ ኡመር አሊ እና አንዳርጌ ታደሰ በመቅደላ ወረዳ ማሻ ከተማ አዲስ በተመሰረተው የከተማዋ ክፍል ነዋሪ ሲኾኑ የመሰረተ ልማት ችግሮች እንደነበሩባቸው ተናግረዋል፡፡ በተለይም የመንገድ መሰረተ ልማት ባለመኖሩ እና አካባቢው ጥቁር አፈር በመኾኑ ዝናብ ሲጥል በጭቃ ይቸገሩ እንደነበር ነው ያነሱት፡፡
የመብራት አገልግሎት አለመኖርም ሌላኛው ችግር እንደነበር ነዋሪዎች ያለፉትን ዓመታት አስታውሰው ነግረውናል። በማኅበረሰቡ እና በመንግሥት ትብብር አሁን ላይ የውስጥ ለውስጥ የጠጠር መንገድ በመሠራቱ እና የመብራት መሰረተ ልማት በመሟላቱ ችግሮቻቸው እንደተቀረፉላቸው ገልጸዋል፡፡
በቀጣይም በሚከናወኑ ልማቶች የማኅበረሰብ ተሳትፎን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡የመቅደላ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ አብዱረህማን ይመር በ21 ሚሊዮን ብር ወጭ የተሠሩት መሠረተ ልማቶች ግንባታቸው ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል ነው ያሉት። ከዚህ ውስጥ 13 ሚሊዮን ብሩ በኅብረተሰብ ተሳትፎ የተገኘ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
በ12 ሚሊዮን ብር የተገነባው 8 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ መንገድ እና ትራንስፎርመርን ጨምሮ የመብራት ዝርጋታ ሥራ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት ኾኗል ብለዋል፡፡
የደቡብ ወሎ ዞን ከተማና መሠረተ ልማት መምሪያ ኀላፊ መርከቡ ታረቀ በበኩላቸው በዞኑ ከ408 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ በጀት 90 የከተማ መሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ለመሥራት በበጀት ዓመቱ ታቅዶ እየተሠራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
እቅዱን ለመተግበር የጸጥታ ችግር እንቅፋት እንደኾነ ያነሱት መምሪያ ኀላፊው ከችግሩ ጎን ለጎን ሥራዎች መከናወናቸው በፈተና ውስጥ ኾኖም ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሥራ መሥራት መቻልን ያሳያል ነው ያሉት፡፡የመቅደላ ወረዳ ማሻ ከተማ ለዚህ ማሳያ መኾኑን ያነሱት ኀላፊው በቀሪ ጊዜያቶች የበጀት ዓመቱን እቅድ ለመፈጸም መሥራት ይጠበቃል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀን አምባቸው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!