ከሰላም እና ደኅንነት ሥራ ጎን ለጎን የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ እንደሚገኝ የደቡብ ወሎ ዞን አስታወቀ፡፡

19

ባሕር ዳር: የካቲት 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በ2016 የበጋ መስኖ ስንዴ የታቀደውን ምርት ለማምረት የሚያስችል ቁመና ላይ እንደሚገኝ የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታውቋል፡፡በደቡብ ወሎ ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ የተመራ ልዑክ በተንታ እና መቅደላ ወረዳ በበጋ መስኖ ስንዴ እየለሙ ያሉ አካባቢዎችን ተዘዋውሮ ተመልክቷል፡፡

የተንታ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር አረጋ እንድሪስ እና ከተማው ሙሐመድ ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ በበጋ መስኖ ስንዴ የተሻለ ምርት ማግኘታቸውን ነግረውናል፡፡

በመቅደላ ወረዳ የ012 ቀበሌ የመስኖ ልማት ተጠቃሚ አርሶ አደር ጎሹ ስንደው ባለፈው ዓመት በሚያለሙት አንድ ሄክታር ማሳ ላይ የተሻለ ምርት ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡

በዚህ ዓመትም ምርጥ ዘር እና ማዳበሪያ በወቅቱ እንደደረሳቸው የተናገሩት አርሶ አደሮቹ የስንዴ ቡቃያው በመልካም ቁመና እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

የተባይ አሰሳ እና አረም በወቅቱ እያከናወኑ አሚኮ ያገኛቸው አርሶ አደሮች የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ አስረድተዋል፡፡የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ አህመድ ጋሎ 26 ሺህ 600 ሄክታር መሬት በዘር መሸፈን እንደተቻለ ገልጸዋል፡፡

ኀላፊው 30 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ቀርቦ 27 ሺህ ኩንታል ጥቅም ላይ ውሏል ብለዋል፡፡ በዚህም 719 ሺህ ኩንታል የስንዴ ምርት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡የደቡብ ወሎ ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ አሊ ይማም ከሰላም እና ጸጥታ ተግባሩ ጎን ለጎን የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በትኩረት እየተሠራ ያለ ተግባር እንደኾነ ተናረዋል፡፡

ከባለፈው ዓመት ተሞክሮ በመነሳት ለመስኖ ስንዴ ልማት የአርሶ አደሩ ተነሳሽነት እያደገ መምጣቱን የተናሩት ምክትል አሥተዳዳሪው በመንግሥት በኩል ያለው የድጋፍ እና ክትል ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀን አምባቸው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ልማት ባንክ ጋር ያላት አጋርነት ውጤታማ ኾኖ ቀጥሏል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next articleበመቅደላ ወረዳ ከ21 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገባቸው የተለያዩ የመሰረተ ልማት ሥራዎች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ኾኑ፡፡