
ባሕር ዳር፡ የካቲት 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል መንግሥት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው የተመለሱ ከ10 ሺህ 500 በላይ ታጣቂዎች የተሃድሶ ሥልጠና ወስደው ወደ ማኅበረሰቡ መቀላቀላቸውን በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አስተባባሪ እና የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ ደሳለኝ ጣሰው አስታውቀዋል።
አቶ ደሳለኝ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት በተከናወነው የሕግ ማስከበር ሥራ ክልሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሰላም እና ጸጥታ ሁኔታ ውስጥ ይገኛል።
ክልሉ በተሟላ ሰላም ላይ መኾኑን ማረጋገጥ የሚቻለው ሕዝቡ በነጻነት ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ጉዳዮችን ማከናወን ሲችል እንደኾነ ጠቅሰው ከዚህ አንጻር አሁንም ሰፊ ሥራ መሥራት ይጠይቃል ብለዋል።
የመከላከያ ሠራዊት እና የክልሉ የጸጥታ አካላት በጋራ በመኾን ጽንፈኛ እና ዘራፊው ቡድን ጥፋት ለመፈጸም ያደረገውን ሙከራ ማክሸፍ መቻሉን ገልጸዋል። የክልሉ መንግሥት ችግሮችን መፍታት የሚቻለው በሰላማዊ መንገድ መኾን እንደሚገባ አቋም ወስዶ እየሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
በዚህም በተደጋጋሚ በተደረገ የሰላም ጥሪ እና በሕግ ማስከበር ወቅት በቁጥጥር ስር የዋሉ ታጣቂዎች ስለሰላም ዋጋ አስፈላጊነት በተሰጣቸው የተሃድሶ ሥልጠና እራሳቸውም የሰላም ዘብ ለመኾን ኀላፊነት እየወሰዱ ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ ማድረግ መቻሉን አብራርተዋል።
እስከ አሁን በተደረገ ጥረት ከ10 ሺህ 500 በላይ ታጣቂዎች የተሃድሶ ሥልጠና ወስደው ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ ማድረግ እንደተቻለ አስታውቀዋል። መንግሥት ሁሉንም ችግሮች በሰላም እና በውይይት ለመፍታት ዝግጁ መኾኑን የገለጹት አቶ ደሳለኝ፤ ከዚህ ውጭ ያለው መንገድ ተገቢነት እንደሌለው ገልጸዋል።
በጥፋት መንገድ ችግር ውስጥ የገባው ጽንፈኛ እና ዘራፊ ቡድን ሕዝቡን በመዝረፍ እና ሰዎችን በማገት የውንብድና ሥራ ላይ ተሰማርቶ እንደሚገኝ አስረድተዋል። ባለፉት ወራት በታጣቂ ቡድኑ በርካታ የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተቋማት ላይ በደረሰ ውድመት ከ15 ቢሊዮን ብር በላይ ጉዳት እንደደረሰ በዳሰሳ ጥናት መረጋገጡንም ገልጸዋል።
መንግሥት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገባውን ማዳበሪያ ሳይቀር ቡድኑ እየዘረፈ ለግል ጥቅሙ እያዋለ መኾኑን አውስተው፤ ይህንን ከሕዝብ ጥቅም በተቃራኒ የኾነ ተግባር የሚፈጽመውን ቡድን ሕዝቡ አምርሮ ሊታገለው ይገባል ብለዋል።
ጽንፈኛ እና ዘራፊ ቡድኑ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሕዝቡን ለተደራራቢ ችግር እየዳረገ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል። የሕዝብን ጥቅም አስጠብቃለሁ ብሎ የሚታገል አካል ሕዝብን ሊዘርፍ እና ሊቀማ ፈጽሞ አይችልም ያሉት አቶ ደሳለኝ ይህንን የአማራ ክልል ሕዝብ እሴት ያልኾነ ተግባር መታገልና ማስቆም እንደሚገባ አስገንዝበዋል። የክልሉ መንግሥት የተገኘውን ሰላም በማጽናት ሕግ የማስክበር ሥራውን የበለጠ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!