
ባሕር ዳር: የካቲት 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ወጣቶች ኢትዮጵያን ለመበተን የሚሠሩ ኃይሎችን አጀንዳ ተቀባይ ከመኾን በመጠንቀቅ ለአንድነት ሊቆሙ እንደሚገባ ተጠይቋል። በአማራ ክልል ከታወጀው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር በተያያዘ በተለያዩ ምክንያቶች ተጠርጥረው የተሐድሶ ሥልጠና ሲወስዱ የቆዩ ወጣቶች ሥልጠናቸውን አጠናቅቀዋል።
በማጠናቀቂያ መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የሰሜን ምዕራብ እዝ ጠቅላይ መምሪያ የባሕር ዳር እና አካባቢው ኮማንድ ፖስት ተወካይ ኮሎኔል ተስፋየ ኤፍሬም ባለፉት ወራት በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ መደፍረስ ማኅበረሰቡ ችግር ውስጥ መግባቱን ገልጸዋል።
በኃይል ፍላጎትን ለማሳካት የሚደረግ እንቅስቃሴ አክሳሪ መኾኑን ያነሱት ኮሌኔሉ የሚነሱ ጥቃቄዎችን በሰላማዊ መንገድ መፍታትን ባሕል ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል። ወጣቶችን በመጠቀም ኢትዮጵያን ለመበተን የሚሠሩ የውጭ እና የውስጥ ጠላቶች አሉ፤ ይህንን በመረዳት የጥፋት አጀንዳዎችን ከመቀበል መቆጠብ ይገባል ሲሉም ለወጣቶች መልእክት አስተላልፈዋል።
የፌዴራል ፖሊስ ሰሜን ምዕራብ ሬጅመንት አምስት አዛዥ ኮማንደር ደሳለኝ ገላው እንዳሉት ባለፉት አራት ዓመታት በተፈጠረው ችግር ምክንያት ሀብት እና ንብረት ወድሟል፤ የሰው ሕይወትም ጠፍቷል። በግጭቱ ምክንያት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎቸ ይበልጥ ተጎጅ ኾነዋል ብለዋል። የሚነሱ ጥያቄዎች በሙሉ በሠለጠነ መንገድ እንዲፈቱ ሰላማዊ መንገድን አማራጭ አድርጎ መሥራት ይገባል ብለዋል።
የባሕር ዳር ከተማ ማረሚያ ቤት መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር ተሻገር ባየ ማረሚያ ቤቶች ታራሚዎችን አስተምሮ ወደ ማኅበረሰቡ በመቀላቀል ራሳቸውን ብሎም ሀገራቸውን እንዲለውጡ አላማ አድርገው እየሠሩ ይገኛሉ ብለዋል። ሠልጣኞችም ወደ ማኅበረሰቡ ሲቀላቀሉ ለክልሉ ሰላም ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ አብርሃም አሰፋ ባላፉት ዓመታት በተከሰተው ጦርነት በክልሉ ላይ ከፍተኛ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሳራ መድረሱን ገልጸዋል። በአማራ ክልል ሕዝብ ጥያቄዎች ላይ ልዩነት አለመኖሩን ያነሱት ኀላፊው ጥቃቄዎችን ለመፍታት ግን ኃይል አማራጭ አለመኾኑን ገልጸዋል። የሕዝብን ጥያቄ ነጥቆ የግል የፖለቲካ ማሳኪያ መንገድ ማድረግም ተገቢ አለመኾኑን ተናግረዋል። በመኾኑም በክልሉ የሚነሱ ጥያቄዎች በሰላም እንዲፈቱ ወጣቶች አጋዥ ሊኾኑ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!