
አዲስ አበባ: የካቲት 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ) “የጤና አገልግሎት ጥራትን፣ ደኅንነትን እና ፍትሐዊነትን ለማሻሻል የጤና ሥርዓት ኢኖቬሽንን ማጎልበት” በሚል መሪ መልእክት በጤና ሚነስቴር የተዘጋጀው 8ኛው ሀገር አቀፍ የጤና ክብካቤ ጥራት ጉባኤ ተጠናቅቋል።
በጉባኤው በአነስተኛ ፍይናንስ፤ ጥራት ያለው የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ኢኖቬሽን የሚጫወተው ሚና ምን መኾን አለበት በሚለው ርእሰ ጉዳይ ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡
የጉባኤው የሁለቱ ቀን ውሎም ተገምግሞ መወሰድ ያለባቸው ማሻሻያዎች እና መቀጠል ያለባቸው ጉዳዮች ላይም ማጠቃለያ ቀርቧል፡፡
ጥራት ያለው እና ደኅንነቱን የጠበቀ ፍትሐዊ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን እና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በፈጠራ የታገዙ አዳዲስ የተሻሻሉ አሠራሮችን ማጎልበት እና መጠቀም እንደሚገባ ነው የቀረበው ።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ እንዳሉት የጤና አገልግሎት ጥራትን፣ ደኅንነትን እና ፍትሐዊነትን ለማሻሻል በጤና ኢኖቬሽን ዙሪያ የተገኙ ውጤቶችን ማዝለቅ እና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እና ኢኖቬሽኖችን ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
በጤናው ዘርፍ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እና የኢኖቬሽን ውጤቶችን የማላመድ እና የማስተዋወቅ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል።በጉባኤው ላይ የተገኙት የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ.ር) የጤና ኢኖቬሽን ፈጠራዎች በጤናው ዘርፍ ለአገልግሎት ጥራት እና ፍትሐዊነት አስፈላጊ እንደኾኑ ተናግረዋል፡፡ ለዚህም የጤና ክብካቤ ጥራትን፣ ደኅንነት እና ፍትሐዊነትን ከማሻሻል አንጻር የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በትኩረት እንደሚሠራ ዶክተር በለጠ አስረድተዋል። ጉባኤው ከየካቲት 26/2016 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ ቆይቷል።
ዘጋቢ፡- ቤቴል መኮንን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!