“ያለፉት ስድስት ወራት በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ትልቅ እመርታ የታየበት ነው” አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ

41

ባሕርዳር: የካቲት 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ያለፉት ስድስት ወራት በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነትና የዲፕሎማሲያዊ መስክ ትልቅ እመርታ የታየባቸው መኾናቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ገለጹ።

በተለይም ከልማትና ከእድገት መሻቶቻችን ጋር ተያይዞ አዳዲስ የዓለም የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ስብስቦች አካል ለመኾን ባደረግነው ጥረት የብሪክስ አባል መኾናችን ትልቅ እርምጃ ነው ብለዋል። ይህ የዲፕሎማሲ ጥረት አባል ለመኾን ብዙ ሥራ የጠየቀ፣ የብዙዎችን ይኹንታ ያገኘም መኾኑንም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ በታሪክ አጋጣሚ እና ስብራት የወደብ ባለቤት አይደለችም ያሉት ሚኒስትሩ ቀጣናው ላይ የተለያየ ርዕዮት ያላቸው ሀገራት የሰፈሩበት እንደመኾኑ እንደ ሀገር የእነዚህን የተለያየ አመለካከት ያላቸው ሀገራት ችግሮች ልንኾን አንችልም ብለዋል።

ጉዳዩ ከቀጥታ ብሔራዊ የጸጥታ ጉዳያችን እና ከህልውናችን ጋር የተያያዘ እንደኾነ ገልጸው የባህር በር መጠየቅ ለኢትዮጵያ ሕጋዊም ፍትሐዊም ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በተለያየ የሽግግር ኡደቶች ውስጥ ኾና እንኳን እድገቷ ከፍ እያለ መኾኑን ያስረዱት አምባሳደር ታዬ እድገቱን ተከትሎ ከሌሎች ሀገሮች ጋር ያለን ግንኙነት ከፍ ይል ዘንድ በዓለም አቀፍ ንግድ ውስጥ በስፋት መግብት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ይሄንን ለማድረግ ደግሞ የባህር በር ጉዳይ ወሳኝ በመኾኑ ኢትዮጵያ ፍላጎቷን ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ለማስረዳት የጥያቄውን ተገቢነት ለማስገንዘብ የሄደችበት መንገድ ትልቅ እመርታ የታየበት መኾኑንም አስረድተዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት በኢትዮጵያ ላይ የተለያዩ ተጽዕኖዎች ተከስተዋል ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከጸጥታው ምክር ቤት ጀምሮ የነበሩ ውጣ ውረዶችን ማለፍ መቻሉንም ጠቁመዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“መዲናችን ከከተማ መስፋፋት ጋር የሚመጣ ፍላጎትን የሚያጎሉ ወሳኝ የሆኑ የእድገት እና የለውጥ ሂደት ውስጥ ትገኛለች” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next article“የጤና አገልግሎቱን ለማሻሻል በጤና ኢኖቬሽን የተገኙ ውጤቶችን ማዝለቅ እና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል” ጤና ሚነስቴር