“አዲስ የፍትሕ መዋቅራዊ ለውጥ ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቷል” የፍትሕ ሚኒስቴር

30

ባሕር ዳር: የካቲት 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በተለያዩ የመንግሥት አሥተዳደሮች ሲሠራባቸው የቆዩ የፍትሕ ዘርፍ ማሻሻያዎች ጥንካሬ እና ድክመትን በመለየት አዲስ የፍትሕ መዋቅራዊ ለውጥ ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ.ር) ገለጹ።

የፍትሕ ሚኒስትር ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ የሚኒስቴሩን የ2016 ሁለተኛው ሩብ ዓመት የሥራ አፈፃፀም አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል።በማብራሪያቸውም በተለያዩ የመንግሥት አሥተዳደሮች ሲሠራባቸው የቆዩ የፍትሕ ዘርፍ ማሻሻያዎች ጥንካሬ እና ድክመትን በመለየት አዲስ የፍትሕ መዋቅራዊ ለውጥ ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቷል ብለዋል።

በሚኒስቴሩ ከፍትሕ አኳያ የጸጥታ ጉዳይ እና የፍትሕ ዘርፍ ማሻሻያ ጉዳዮች ትኩረት ተሰጥቷቸዋል ነው ያሉት፡፡በፍትሕ ዘርፉ የሽግግር ፍትሕ እና የፍትሕ ሥርዓት መዋቅራዊ ለውጥ ፍኖተ ካርታ ትኩረት የተሰጣቸው ጉዳዮች መኾናቸውንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

በዚህም ጸጥታውን በሚመለከት ኢትዮጵያ ሽግግር ውስጥ እንደመኾኗ የሽግግር ፍትሕን መከተል ተገቢ መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡በተለያዩ የመንግሥት አሥተዳደሮች ሲሠራባቸው የቆዩ የፍትሕ ዘርፍ ማሻሻያዎች ጥንካሬ እና ድክመት በመለየት አዲስ የፍትሕ መዋቅራዊ ለውጥ ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን ነው የተናገሩት፡፡

በፍኖተ ካርታው ላይ ከክልሎች ጋር በመወያየት ወደ ተግባር እየተገባ መኾኑን እና በአንዳንድ ክልሎች ላይ ተተግብሮ ለውጥ ማሳየት መጀመሩንም ዶክተር ጌዲዮን አስታውቀዋል፡፡

መዋቅራዊ ለውጥ ፍኖተ ካርታው 10 የትኩረት አቅጣጫዎች ያሉት ሲኾን ከእነዚህም ውስጥ በበጀት ዓመቱ ትኩረት ተደርጎ ሊሠራበት የታሰበው ማኅበረሰብ ተኮር የፍትሕ አገልግሎት መኾኑን ተናግረዋል፡፡የመዋቅራዊ ለውጡ እና የሽግግር ፍትሕ ፍኖተ ካርታ ፖሊሲ ትግበራ በፍትሕ ዘርፉ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ እንደኾነም ነው ሚኒስትሩ ያስታወቁት፡፡ኢዜአ እንደዘገበው ግጭትን የመከላከል እና የመፍታት አቅምን ማዳበር ላይ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች መኖራቸውንም ዶክተር ጌዲዮን አብራርተዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“የኤሌክትሪክ ኃይልን በሽያጭ መልክ በማቅረብ የዲፕሎማሲ አንዱ አካል ለማድረግ እየተሠራ ነው” የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
Next article“መዲናችን ከከተማ መስፋፋት ጋር የሚመጣ ፍላጎትን የሚያጎሉ ወሳኝ የሆኑ የእድገት እና የለውጥ ሂደት ውስጥ ትገኛለች” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)