“የኤሌክትሪክ ኃይልን በሽያጭ መልክ በማቅረብ የዲፕሎማሲ አንዱ አካል ለማድረግ እየተሠራ ነው” የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

28

አዲስ አበባ: የካቲት 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ኢትዮጵያ በኢነርጂ እና የአቪየሽን ዲፕሎማሲ ቀጣናዊ ትስስር ለመፍጠር ትኩረት ሰጥታ እየሠራች መኾኑ ተገልጿል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም (ዶ.ር) በወቅታዊ እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዙሪያ በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያ በቀጣናው በኢነርጂ እና አቬሽን ዲፕሎማሲ ጠንካራ ትስስር እንዲፈጠር እየሠራች መኾኑን አንስተዋል።

ቃል አቀባዩ የሰሞኑ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በኬንያ እና በታንዛኒያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት የተፈረሙ ሥምምነቶች መካከል የኢነርጂ እና አቬሽን ዘርፎች እንደሚገኙበት ገልጸዋል። ይህ መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት መሥጠቱን ያመለክታል ብለዋል።

ቃል አቀባዩ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ኢትዮጵያ በቀጣናዊ ትስስር እና ትብብር ላይ ያላት ተፈላጊነት ከፍተኛ መኾኑን ያረጋገጠ ስለመኾኑም አብራርተዋል። ጉብኝቱ ኢትዮጵያ ለቀጣናዊ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ አስፈላጊ አጋር መኾኗ የታየበት እንደኾነም አምባሳደር ዶክተር መለስ ዓለም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ለኬንያ የሰጠችው የኃይል ሽያጭ በደቡባዊ እና ምዕራብ አፍሪካ የሚሻገር የኢነርጂ ትስስር የአህጉሩ ፕሮጀክት አካል ይኾናል ብለዋል። ኢትዮጵያ በቀጣይ ለዳሬሰላም 400 ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ ኃይል በሽያጭ መልክ ለማቅረብ መስማማቷ ኢነርጂ የዲፕሎማሲ አንዱ አካል መኾኑን እንደሚያመላክት አስረድተዋል።

በአቪየሽን የዲፕሎማሲ መስክ በበረራ ያለውን ትብብር ይበልጥ ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ስምምነቱ ያግዛል ነው የተባለው። ከአውሮፓውያኑ 2016 እስከ 2023 ድረስ 75 የታንዛኒያ አብራሪዎች እና 25 በዘርፉ የሚሠሩ የበረራ ቴክኒሺያኖች በኢትዮጵያ ሥልጠና ማግኘታቸውን ጠቅሰዋል። ቃል አቀባዩ ሌሎች በሳምንቱ በሚኒስትር ዴኤታዎች የተከናወኑ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴዎችን በተመለከተም ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ዘጋቢ፡- ናዝሬት ክንድሽ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበጎጃም ያለው የሕግ ማስከበር ዘመቻ በሚፈለገዉ መንገድ እየሄደ እንደኾነ የጎጃም ኮማንድ ፖስት አስታወቀ፡፡
Next article“አዲስ የፍትሕ መዋቅራዊ ለውጥ ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቷል” የፍትሕ ሚኒስቴር