
ባሕር ዳር: የካቲት 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በጎጃም ያለው የሕግ ማስከበር ዘመቻ በሚፈለገዉ መንገድ እየሄደ እንደኾነ የጎጃም ኮማንድ ፖስት አስታውቋል፡፡
በጎጃም ኮማንድፖስት ሥር የሚገኘው ክፍለ ጦር እና የአማራ ክልል የፀጥታ ኃይል በመቀናጀት የተሰማሩበትን ሕግ የማስከበር ግዳጅ በተሳካ ሁኔታ እንደቀጠለ ታውቋል።
የክፍለ ጦሩ አዛዥ ሌተናል ኮረኔል ድባቤ አበራ ክፍለ ጦሩ ወደ ቁጭ ያሰማራው አምስተኛ ሬጅመንት ግዳጁን ወደ ሰርተከዝ በማስፋት ለሽብር ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ጽንፈኞችን አስወግዶ የተለያዩ መሣሪያዎችን እና ታጣቂዎችንም ማርኳል ብለዋል።
በዚህ ኦፕሬሽን የቁጭ ፖሊስ እና ሚሊሻ ጭምር ከሠራዊታችን ጎን በመሠለፍ ሚናቸውን ተወጥተዋልም ተብሏል። ወደ ሰከላ አካበቢ የተንቀሳቀሱት የክፍለ ጦሩ አንደኛ እና አራተኛ ሬጅመንት እና የአማራ ክልል አድማ መከላከል ጽንፈኛው ቡድን ከሕዝብ ዘርፎ ጫካ በመደበቅ ከፍተኛ ገንዘብ የጠየቀበትን የጭነት መኪናም አስመልሰዋል።
ሌተናል ኮረኔል ድባቤ እንደተናገሩት ክፍለ ጦሩ እና የአማራ ክልል የፀጥታ ኃይል በመቀናጀት ጽንፈኛው ቡድን ወደየተደበቀበት በመሠማራት እና በማሰስ ሕግ የማስከበር ሥራውን አጠናክረው ይቀጥላሉ ሲል የአማራ ኮሙኒኬሽን የጎጃም ኮማንድፖስትን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!