አምሪፍ ሄልዝ አፍሪካ ከባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ጋር በመቀናጀት በጤናማ የወጣቶች ሥብዕና ግንባታ ዙሪያ ያሠለጠናቸውን ተማሪዎች አስመርቋል፡፡

32

ባሕር ዳር: የካቲት 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአምሪፍ ሄልዝ አፍሪካ የአማራ ክልል አስተባባሪ ደሴ ካሳ በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ እንደተናገሩት ሀገር ተረካቢ ወጣት ተማሪዎች በአቻ ግፊት እና መሰል ምክንያቶች ለጉዳት ሲጋለጡ ማየት እየተለመደ መጥቷል፡፡ ስለኾነም በርካታ ዜጎችን እያጣን እንገኛለን ብለዋል።

አምሪፍ ሄልዝ አፍሪካ የማኅበረሰብ ግንባታ ጠንቅ ድርጊትን በመከላከል ጤናማ የወጣቶች ስብዕና እንዲረጋገጥ የሚያስችሉ የሥነ ተዋልዶ ጤና፣ የአቻ ግፊት፣ የሱስ፣ ጎጅ ልማዳዊ ድርጊት፣ የኤች አይ ቪ ኤድስ እና ላልተፈለገ እርግዝና መጋለጥን የተመለከቱ ሥልጠናዎችን መስጠቱን አስተባባሪው ጠቅሰዋል፡፡

“ማህረቤን” በሚል የመነሻ ሃሳብ ለኹለተኛ ዙር የሠለጠኑ ተማሪዎችን ማስመረቁንም ተናግረዋል።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ኃይለማርያም እሸቴ በምረቃው ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት አምሪፍ ሄልዝ አፍሪካ በተማሪ ወጣቶች ላይ ሊከሰቱ የሚችሉ የተለያየ ጥቃቶችን ለመከላከል እያደረገ ያለው ብርቱ ጥረት የሚደነቅ እንደኾነ ተናግረዋል።

የሰለጠኑ ተማሪዎችም ዕውቀታቸውን ለራሳቸው ብቻ ሳይኾን ለሌሎች ትምህርት ቤቶች እና አቻዎቻቸው ማካፈል እንዳለባቸው ገልጸዋል። አጋር እና ባለድርሻ አካላትም ለሥራው መሳካት ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ አቶ ኃይለማርያም አሳስበዋል።

ተመራቂ ተማሪዎች በበኩላቸው የተሰጣቸው ሥልጠና ከራሳቸው አልፎ ለሌሎች ወጣቶች የሚተርፍ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ በተለይም በራስ መተማመን፣ አጋላጭ ጉዳዮችን በመለየት እና የመከላከል ክህሎትን፣ ጎጅ ልማዶችን እና የማኅበረሰብ ልማት ጠንቆችን በሚገባ በመረዳት ለመከላከል አጋዠ አቅም ማግኘታቸውንም ተናግረዋል፡፡

ያገኙትን የንድፈ ሃሳብ እና የተግባር ዕውቀት በተግባር ለመለውጥ መነሳሳታቸውን ገልጸው አምሪፍ ሄልዝ አፍሪካንም አመስግነዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleዓለም አቀፍ አስጎብኚ ድርጅቶች በደንበኞቻቸው የጉዞ ዝርዝር ውስጥ ኢትዮጵያን ማካተት እንዲችሉ ስምምነት ተደረሰ፡፡
Next articleበጎጃም ያለው የሕግ ማስከበር ዘመቻ በሚፈለገዉ መንገድ እየሄደ እንደኾነ የጎጃም ኮማንድ ፖስት አስታወቀ፡፡