
ባሕር ዳር: የካቲት 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ በጀርመን በርሊን እየተካሄደ ባለው ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ኤግዚቢሽን ላይ የቱሪዝም ሃብቶቿን እያስተዋወቀች ነው፡፡ ሁለተኛ ቀኑን በያዘው በዚህ ኤግዚቢሽን ላይ የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ የጉዞ ድርጅቶች እና የሀገራት ተወካዮች ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም ዓለም አቀፍ አስጎብኚ ድርጅቶች ለደንበኞቻቸው ኢትዮጵያን እንደ አማራጭ እንዲያቀርቡ እና በጉዞ ዝርዝራቸው ውስጥ ማካተት በሚችሉበት ጉዳዮች ዙሪያ ተስማምተዋል፡፡
በተጨማሪም ከተለያዩ ተቋማት ጋር በቱሪዝም ፕሮሞሽን እና ማርኬቲንግ ዙሪያ በጋራ ለመሥራት የሚያስችል ውይይት ተደርጓል::
ይህ በየዓመቱ የሚዘጋጀው ኤግዚቢሽን በመላው ዓለም የሚገኙ ስመጥር የቱሪዝም ኩባንያዎች እና ሀገራት ያላቸውን መዳረሻ እና የቱሪዝም አገልግሎት የሚያስተዋውቁበት መድረክ ነው። ኢትዮጵያም በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት እያከናወነች ያለችውን የመዳረሻ ልማት እና የቱሪስት መስህቦች እያስተዋወቀች እንደምትገኝ የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!