“ረመዳን እና ዐብይ ጾምን በመረዳዳት እና ለሀገር ሰላም በመጸለይ ልናሳልፍ ይገባል” የሃይማኖት አባቶች

36

ደብረ ማርቆስ: የካቲት 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ የመቻቻል፣ የፍቅር እና የአብሮነት ተምሳሌት ኾና ለዘመናት የቆየች ሀገር ናት፡፡ ይህ የመቻቻል እና የአብሮነት ባሕል በተለይ በተለያዩ ሃይማኖቶች ግንኙነት ላይ ጎልቶ የሚታይ በመኾኑ ሀገራችን በብዙ ሀገሮች ዘንድ በምሳሌነት እንድትጠራ አድርጓታል፡፡

የረመዳን እና ዐብይ ጾምን መገጣጠም ምክንያት በማድረግ ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉት በደብረ ማርቆስ ከተማ የእንድማጣ መስጂድ ኢማም ሱሌማን ደሴ እና በቦሌ መስቀልማ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስትያን የብሉያትና ሐዲሳት መምህሩ ለዓለም ብርሃኑ የየእምነቱ ተከታዮች የየሀይማኖቶቹ አስተምህሮ በሚያዘው መሰረት በመረዳዳት እና ለሀገር ሰላም በመጸለይ ፆሙን ሊያሳልፉ እንደሚገባ አባታዊ ምክራቸን ለግሰዋል፡፡

ረመዳን ቅዱስ ወር ነው ሲባል ያለው ለሌለው በማካፈል፣ በመተዛዘን፣ በጎና መልካም ተግባራትን በመፈጸም ለእስልምና እንዲሁም ለነብዩ መሐመድ (ሰ ዐ ወ) አስተምህሮ መገዛትን በተግባር መግለጽ ይገባል ብለዋል ኢማም ሱሌማን ደሴ።

በቦሌ መስቀልማ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስትያን የብሉያትና ሀዲሳት መምህሩ ለዓለም ብርሃኑ በበኩላቸው አሁን ላይ የገጠመንን ፈተና መሻገር የምንችለው በሃይማኖታችን በመጽናት አንድ ሆነን ስንቆም ነው ብለዋል፡፡ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠውን ታላቁን የዐብይ ጾም ስናሳልፍ በሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ለድርቅና ለረሀብ የተጋለጡትን እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች የተፈናቀሉትን ወገኖች በማሰብና ካለን በማካፈል ሊኾን ይገባልም ሲሉ በአጽንኦት ተናግረዋል።

ሀገራችን በሰላም እጦት በብርቱ እየተፈተነች ያለችበት ወቅት ላይ የምንገኝ በመኾኑ የሃይማኖት አባቶች፣ ምዕመናን እና በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት አካላት ሁሉ ለሰላምን መስፈን የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባልም ብለዋል የሃይማኖት አባቶቹ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገራችን እየታዬ ያለው ሃይማኖትን እና የሃይማኖት ተቋማትን የግጭት እና የመከፋፈል መሣሪያ የማድረግ ዝንባሌ ኀላፊነት የጎደላቸው አካላት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ነው ብለዋል። ይህም ከሃይማኖት መርህም ሆነ ተቋማቱ ከተቋቋሙበት ዓላማ ያፈነገጠ በመሆኑ በዚህ ድርጊት ውስጥ ተሳትፎ ያላቸው አካላት ሊታረሙ ይገባል ብለዋል።

መጾም፣ መጸለይ እና ሌሎች ሃይማኖታዊ ተግባራትን መፈጸም የሚቻለው ከምንም በላይ ሀገር ሰላም ሲትኾን ነውና ሁሉም በየሃይማኖቱ ለሰላም መትጋትና ለሰላም ተባባሪ መኾን ይገባዋል ሲሉም የሃይማኖት አባቶቹ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ባለፉት ስድስት ወራት በሀገሪቱ 1 ሺህ 536 አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች የማምረት ሥራ ጀምረዋል” አቶ መላኩ አለበል
Next articleዓለም አቀፍ አስጎብኚ ድርጅቶች በደንበኞቻቸው የጉዞ ዝርዝር ውስጥ ኢትዮጵያን ማካተት እንዲችሉ ስምምነት ተደረሰ፡፡