“ባለፉት ስድስት ወራት በሀገሪቱ 1 ሺህ 536 አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች የማምረት ሥራ ጀምረዋል” አቶ መላኩ አለበል

34

ባሕር ዳር: የካቲት 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በ2016 በጀት ዓመት ስድስት ወራት በሀገሪቱ 1 ሺህ 536 አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች የማምረት ሥራ መጀመራቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተገኙበት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የ2016 የሁለተኛው ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግመገማ እየተካሄደ ነው።የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል የግምገማው ሂደት ትኩረት ካደረገባቸው ኢኮኖሚያዊ መስኮች መካከል አንዱ የኢንዱስትሪ ዘርፉ አፈጻጸም መኾኑን ገልጸዋል።

የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም በተለያዩ ችግሮች ደካማ እንደነበር ጠቅሰው በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በስፋት ወደ ምርት አንዲገቡ መደረጉን አስታውሰዋል።በ10 ዓመቱ መሪ የልማት እቅድ እና በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በተወሰዱ እርምጃዎች የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ወደ 56 ነጥብ 4 በመቶ ከፍ ማለቱንም ገልጸዋል።

ከፋይናንስ፣ ከጥሬ እቃ አቅርቦት፣ ከሰው ኃይል፣ ከገበያ ትስስር፣ ከኤሌክትሪክ እና መሰል መሠረተ ልማቶች ማሟላት አኳያ ያሉ ችግሮችን በተቀናጀ መንገድ በመፍታት በውጤቱ የማመረት እቅም ማደጉን ተናግረዋል።

የፍጆታ ፍላጎት እየጨመረ በመምጣቱ ለወጪ ንግድ ብቻ ሳይኾን ገቢ ምርት መተካት ላይ የተሰጠው ትኩረት በግምገማው በአዎንታዊ አፈጻጸም መነሳቱን ጠቅሰዋል።በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት በተኪ ምርት 1 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 994 ሚሊዮን ዶላር መሳካቱን ጠቅሰው አፈጻጸሙም 93 በመቶ መኾኑን አንስተዋል።

በግማሽ ዓመቱ 67 የውጭ ባለሃብቶችን በኢንዱስትሪ ዘርፉ በኢንቨስትመንት ለመሳብ ታቅዶ 127 ባለሃብቶች ወደ ኢንቨስትመንት እንዲገቡ መደረጉንም ገልጸዋል።ከሀገር ውስጥ ደግሞ 2 ሺህ 300 አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን ወደ ኢንቨስትመንት ለማስገባት ታቅዶ 1 ሺህ 490 ያህል ወደ ዘርፉ መሰማራታቸውን ተናግረዋል።

በኢንቨስትመንት ከማሰማራት ባለፈ ባለፉት ስድስት ወራት የውጭ እና ሀገር በቀል ኢንዱስትሪዎች ወደ ምርት እንዲገቡ በተሠራው ሥራ 1 ሺህ 536 አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች ማምረት መጀመራቸውን ጠቅሰዋል።

በኢንዱስትሪው ዘርፍ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት ለ142 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ ለ121 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩንም ገልጸዋል።
በመድረኩ ከተዳሰሱ የዘርፉ ተግባራት መካከል የኢትዮጵያ ታመርት ንቅናቄ አፈጻጸም ይገኝበታል ያሉት ሚኒስትሩ ንቅናቄው ባለፉት ሁለት ዓመታት ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ ነው ብለዋል።

የሀገሪቱን ሃብት በማስተዋወቅ፣ የገበያ ትስስር በመፍጠር፣ ለሀገር ውስጥ ምርት ቅድሚያ በመስጠት፣ ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ በመፍጠር፣ የቅንጅት ችግሮችን በመፍታት፣ የፖሊሲ ማሻሻያ በማድረግ ረገድ ውጤቶች መመዝገባቸውን አመላክተዋል።

አምራች ኢንዱስትሪው በሀገራዊ ጥቅል ምርት ያለውን ድርሻ ለማሳደግ ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት፣ የመንግሥት ግዥ ለሀገር ውስጥ ምርት ቅድሚያ እንዲሰጥ፣ የፋይናንስ አቅርቦት እንዲስተካከል፣ መሰረተ ልማትን ጨምሮ ምቹ ሁኔታ የመስጠት ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አቅጣጫ መቀመጡን ገልጸዋል።ከወጪ ንግድ አኳያ ዘርፉ ያለው ዝቅተኛ አፈጻጸም እንዲያድግ በልዩ ትኩረት ይሠራል ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ኑሯቸውን በጎዳና ያደረጉ ዜጎችን በማሠልጠን አምራች ዜጋ እንዲኾኑ የተሠራው ሥራ ውጤታማ ነው” የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር
Next article“ረመዳን እና ዐብይ ጾምን በመረዳዳት እና ለሀገር ሰላም በመጸለይ ልናሳልፍ ይገባል” የሃይማኖት አባቶች