
ደብረ ብርሃን: የካቲት 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በደብረ ብርሃን ከተማ ኑሯቸውን ጎዳና ላይ ያደረጉ 253 ዜጎችን የሦስት ወራት የሕይወት ክህሎት ሥልጠና እንዲያገኙ ማድረጉን የከተማ አሥተዳደሩ ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ገልጿል፡፡
አብርሀም አሰፋ ለሦስት ዓመት ከስድስት ወር በጎዳና ሕይወቱን አሳልፏል “ሕይወት አስከፊና መራር ነው” ይላል፡፡ ዛሬ ላይ አብርሃም ከፕሮጀክቱ በሚገኘው የመነሻ ካፒታል የዶሮ ማርባት ሥራን ለመሥራት ነው ያሰበው፡፡
ቀጣይ ባገኘው ሥልጠና የገንዘብ አያያዝ ብልሃት እና የሃብት ማመንጫ መንገዶችን በመከተል ወደ ተሻለ ሕይወት እንደሚደርስ አልሟል፡፡
ኑሯቸውን በጎዳና ያደረጉ ዜጎችን በማሠልጠን አምራች ዜጋ እንዲኾኑ በዓለም ባንክ የሴፍ ትኔት ፕሮግራም 15 ሚሊዮን ብር በጀት ተመድቦ እየተሠራ እንደሚገኝ የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ በለጥሽ ግርማ ተናግረዋል፡፡
ኑሯቸውን በጎዳና ያደረጉ ዜጎችን በማሠባሠብ የሥነ ልቦና እና የሕይወት ክህሎት ሥልጠና አግኝተው በመረጡት የሥራ መስክ እንዲሰማሩ ሙያዊ ሥልጠና በመስጠቱ ለውጦች እንዳሉ ኀላፊዋ ጠቁመዋል፡፡
በወሰዱት ሥልጠና ሙያዊ ክህሎትን ተላብሰው በመረጡት የሥራ መስክ እንዲሰማሩ ለእያንዳንዳቸው 29 ሺህ 560 ብር ለመነሻ እንደሚሰጣቸውም ነው የተናገሩት፡፡
ሠልጣኞቹ በተሰማሩበት የሥራ መስክ ላይ ለቀጣይ 15 ወራት ድጋፍ እና ክትትል እንደሚደረግላቸውም መምሪያ ኀላፊዋ አስገንዝበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አበበች የኋላሸት
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!