
ባሕር ዳር: የካቲት 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ)
በ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት 302 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሤ ገለጹ።ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተገኙበት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የ2016 የሁለተኛው ሩብ ዓመት የሥራ አፈፃፀም ግምገማ እየተካሄደ ነው።
የግምገማው ሂደት ትኩረት ካደረገባቸው መስኮች መካከል አንዱ የገቢ ዘርፉ አፈጻጸም መኾኑን የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሤ ገልጸዋል።በገቢ አሰባሰብ በበጀት ዓመቱ 529 ቢሊዮን ብር እንዲሁም በግማሽ ዓመቱ 312 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ዕቅድ መያዙን አስታውሰዋል።
ከዚህም በስድስት ወራት 302 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ የእቅዱን 96 በመቶ ማሳካት መቻሉን ገልጸዋል።አንዳንድ ቅርንጫፎች ባሉበት አካባቢ ችግር ቢኖርም ይህንን ለማካካስ እየተሠራ ነው ያሉት ሚኒስትሯ ገቢ አሰባሰቡ በፈተናዎች ውስጥ እያለፈም የተሻለ አፈጻጸም አለው ብለዋል።
ከሀገሪቱ የኢኮኖሚ አቅም አንጻር እየተሰበሰበ ያለው ገቢ ዝቅተኛ መኾኑን የጠቀሱት ሚኒስትሯ የታክስ አሥተዳደርን ማሻሻል እና የክልሎችን ገቢ አሰባሰብ አቅም ማሳደግ የቀጣይ ትኩረት ይሆናል ብለዋል።
የኮንትሮባንድ መስፋፋት፣ ሕገ ወጥ ንግድ፣ የሥነ-ምግባር ጉድለት እና ሌብነት የገቢ አሰባሰቡን እየፈተኑት መኾኑን ጠቅሰው ችግሮቹን በዘላቂነት ለመፍታት የጋራ ትግል የሚጠይቅ ነው ብለዋል።
የታክስ አሥተዳደሩን ለማዘመን የሀገር ውስጥ ገቢ በኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ሥርዓት መሰብሰብ መጀመሩን እና በየጊዜው በዲጂታል አማራጭ የሚከፍሉ ግብር ከፋዮች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱንም ሚኒስትሯ ተናግረዋል።
በጉምሩክ በኩል የንግድ ሥርዓቱ ላይ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የገቢ እና ወጪ እቃዎችን የሚያጓጉዙ ተሽከርካሪዎችን በዲጂታል መፈተሽ የሚያስችሉ መሰረተልማቶች እየለሙ ይገኛሉም ብለዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!