“ከ1 ሚሊየን 400 ሺህ ብር በላይ የሚያወጣ የግብርና ግብዓት በጽንፈኛው ቡድን ተዘርፏል” ድረስ ሳሕሉ (ዶ.ር)

23

ባሕር ዳር: የካቲት 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በበርካታ አካባቢዎች በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት የግብርና ምርት እና ምርታማነት ቀንሷል፡፡ ለምርት እና ምርታማነቱ መቀነስ የተፈጥሯዊ ችግሮች መከሰት እና መበራከት እንደምክንያት ቢወሰድም በክልሉ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ጽንፈኞች የፈጠሩት የጸጥታ ችግርም የጎላ ተፅዕኖ አሳድሯል ብለዋል፡፡

በክልሉ ባለፈው የምርት ዘመን የተፈጠረው የግብዓት እጥረት የፈጠረው የምርት እና ምርታማነት መቀነስ ችግር እንዳለ ኾኖ ትልቅ የመልካም አስተዳደር ችግር ምክንያት እንደነበር በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ዘርፍ አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳሕሉ (ዶ.ር) ገልጸዋል፡፡

ዶክተር ድረስ በመግለጫቸው በምርት ዘመኑ ለክልሉ ከ8 ሚሊየን 57 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ተፈጽሞ ቀድሞ ማጓጓዝ ቢጀመርም በክልሉ ታጥቆ የሚንቀሳቀሰው ጽንፈኛ እና ዘራፊ ቡድን በሚፈጽመው ሕገ ወጥ ተግባር ምክንያት ለአርሶ አደሮች በበቂ መጠን ተደራሽ መኾን አልቻለም ብለዋል፡፡ ይህም በክልሉ ሕዝብ እና በአርሶ አደሮ መጻዒ እጣ ፋንታ ላይ መፍረድ ነው ብለዋል፡፡

በአማራ ሕዝብ ስም የሚንቀሳቀስ እና ለአማራ ሕዝብ እታገላለሁ የሚል አካል የግብርና ግብዓት በወቅቱ ለአርሶ አደሮች እንዳይደርስ እንቅፋት መኾን ከግል ጥቅም ያልተላቀቀ ፍላጎት ነው ያሉት ዶክተር ድረስ ፤ ራሱ ሕዝቡ ሕገ ወጦችን በመታገል ግንባር ቀደም መኾን እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

የፖለቲካ ልዩነት እና ቅራኔ ቢኖር እንኳን ችግሮችን በሠለጠነ መንገድ ለመፍታት የሚያስችል ምህዳር ባለበት በዚህ ዘመን ትጥቅ አንግቦ የልማት እንቅስቃሴዎችን መግታት መሠረታዊ ክፍተት ያለበት አካሄድ በመኾኑ ሊታረም የሚገባው እንደኾነ አንስተዋል፡፡ ሕዝቡ ከጸጥታ ኃይሉ ጎን በመሰለፍ አጥፊዎችን ማጋለጥ እና መታገል ይኖርበታል ብለዋል፡፡ የግብርና ግብዓቶችን መዝረፍ በክልሉ ሕዝብ ኅልውና ላይ አደጋ መሰንዘር እንደኾነም አንስተዋል፡፡

ገና ወደ ክልሉ የሚገባ እና ወደብ ላይ የተከዘነ ከ500 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ እንዳለ ያነሱት ዶክተር ድረስ፤ በወቅቱ ለአርሶ አደሩ እንዲደርስ በትብብር መሥራት እና ሰላምን ማስጠበቅ ቅድሚያ የሚሰጠው የትኩረት ነጥብ ነው ብለዋል፡፡

ጽንፈኛው ቡድን ከሰሞኑ “የአፈር ማዳበሪያ በነጻ ስለምናድል ከመንግሥት እንዳትገዙ” በሚል የሚያስተላልፈው መልዕክት ሕዝቡን አዘናግቶ ሲማረር ወደ አልባሌ ትርምስ ይገባል ከሚል ስሌት የመነጨ ነው ብለዋል። ሕዝቡ ከተራ አሉባልታ ወጥቶ በግብርና ሥራው ላይ ሊያተኩር ይገባል ሲሉም አሳስበዋል፡፡

ዘራፊው ቡድን በመንገድ ላይ የሚጓጓዝ፣ በማኅበራት መጋዘን የተከዘነ እና ለአርሶ አደሮች ሊሰራጭ የነበረ የአፈር ማዳበሪያ እና ግብዓት በተደጋጋሚ መዝረፉን ያነሱት ዶክተር ድረስ “ከ1 ሚሊየን 400 ሺህ ብር በላይ የሚያወጣ የግብርና ግብዓት በጽንፈኛው ቡድን ተዘርፏል” ብለዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበኢትዮጵያ ለሚኖሩ ሥደተኞች ብሔራዊ መታወቂያ መሥጠት ተጀመረ።
Next articleበግማሽ ዓመቱ 302 ቢሊዮን ብር ገቢ ተሰብስቧል።