በወቅታዊ ችግር ምክንያት ክፍተት እየታየበት ያለውን ትምህርት ለማስቀጠል የድጋፍ ጥሪ ቀረበ።

55

ባሕር ዳር: የካቲት 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ያስተባበረው የባለድርሻ አካላት ውይይት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

21ኛው የአማራ ትምህርት ክልላዊ ልማት ትብብር (አ.ት.ክ.ል.ት) ፎረም በአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስተባባሪነት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

የፎረሙ ዓላማ በአማራ ክልል ትምህርት ላይ በመንግሥት፣ በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና ዓለም አቀፍ አጋሮች መካከል የተቀናጀ የአሠራር መድረክ መፍጠር ነው። ይህ ትብብር የክልሉን ሕጻናት እና ታዳጊዎች ጥራት ያለው ፍትሐዊ የትምህርት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የሚያግዝ ነው ተብሏል።

ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ውይይቶች በፎረሙ ተካሂደዋል። 21ኛው ፎረምም “ተስፋ ያለው ትውልድ መገንባት፣ ትምህርትን በአደጋ ጊዜ ለማስቀጠል የድጋፍ ጥሪ” በሚል መሪ መልእክት እየተካሄደ ይገኛል።

በመድረኩ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) ባስተላለፉት መልእክት “ውይይቱ ክፍተቶችን ለመሙላት እና ለልጆቻችን ተስፋን ለመፈንጠቅ ታሳቢ ያደረገ ነው” ብለዋል።

የትምህርት ሥራ በኮሮና ቫይረስ እና በሰሜኑ ጦርነት ሲፈተን መቆየቱን ገልጸው አሁን ደግሞ በክልሉ የጸጥታ ችግር እየተፈተነ በመኾኑ ጥራት ያለው የሰው ኃይል ልማት ማፍራት ላይ ጫና አሳድሯል ነው ያሉት።

ዶክተር ሙሉነሽ የትምህርት ቤቶች ደረጃ ዝቅተኛ መኾን አሁን ካለው ችግር ጋር ተዳምሮ ጉድለቱን ስለሚያሰፋ ትብብር እና መደጋገፍ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።
በሰሜኑ ጦርነት ጉዳት የደረሰባቸውን ትምህርት ቤቶች እንደገና ማደስ፣ አሁን ላይ ትምህርት የተቋረጠባቸውን አካባቢዎች ትምህርት ለማስጀመር እና በርካታ ትምህርት ቤቶች የተማሪ ምገባ ስለሚያስፈልጋቸው መደጋገፍ እንደሚያስፈልግ ነው ያብራሩት። በውይይቱ ከፍተኛ አመራሮች እና ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።

ዘጋቢ፡- ድልነሳ መንግሥቴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ግብርና ግን ለአማራ ሕዝብ ከፖለቲካም ከልዩነትም በላይ ነው” ድረስ ሳኅሉ (ዶ.ር)
Next articleበኢትዮጵያ ለሚኖሩ ሥደተኞች ብሔራዊ መታወቂያ መሥጠት ተጀመረ።